የ2012 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክኒያት ትምህርት በመቋረጡ በወቅቱ ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡ ትምህርት ከተጀመረ በኋላም ቢሆን ፈተናናውን በኦንላይን ለመስጠት ታስቦ በሀገር አቀፍ ደረጃ የቅድም ዝግጅት ስራ ሲሰራ ቢቆይም ባለፈው ሳምንት ትምህርት ሚኒስቴር ፈተናው በኦንላይን የማይሰጥና በነበረው የፈተና ስርአት እንደሚሰጥን አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮም በክልል ደረጃ ፈተናውን ውጤታማ ለማድረግ ከዞንና ወረዳ የፈተና ክፍል ሰራተኞች ጋር በባህርዳር ከተማ ፈተናውን አስመልክቶ ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን በጥራትና በአጭር ጊዜ በውጤታማነት እንዳጠናቀቅነው ሁሉ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ባለው አጭር ጊዜ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራ በመስራት በክልላችን ያለመንም ችግር በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የፈተና ጊዜው አጭር በመሆኑ ከዛሬ ጀምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መስራትና ለትምህርት ቤቶችም ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት ለኦን ላይን ፈተና የተመለመሉ ፈታኞች ቀጣዩን ፈተና የሚፈትኑ ሲሆን በየደረጃው ያለው የትምህርት መዋቅር የፈተና ቁሳቁሶች እንዲሟሉ በትኩረት እንደሚሰራም ተነግሯል፡፡
መምህራንና ወላጆችም ተማሪዎችን በስነልቦና እንዲጠነክሩና ባላቸው ጊዜም አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደረጉ የተለመደ ድጋፍ እንዲያደርጉ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከየካቲት29 እስከ መጋቢት 02/2013 ዓ.ም ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በአማራ ክልል ከ82 ሺህ በላይ ተማሪዎችበ249 የፈተና ጣቢያዎች እንደሚፈተኑ ይጠበቃል፡፡