የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከመጋቢት 7-8/2013 ዓ.ም ለሁሉም የዞንና ወረዳ የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ባለሙያዎች የትምህርት ብርሃን ምዘና አስፈላጊነት ዙሪያ በደብረ ታቦርና ወልዲያ ከተሞች የግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠና ሰጠ።
የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ባለፉት አመታት በሀገራችን ሲሰጥ ቢቆይም በቅንጅት መስራቱ ውጤታማ ባለመሆኑ የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ፕሮግራም በአዲስ በሀገር ደረጃ ተጀምሯል።
ጎልማሶች የማንበብ፣የመፃፍና የማስላት ክህሎታቸውን ተጠቅመውና ፍላጎታቸውን መሰረት አድርጎ በዕለት ተዕለት ህይወታቸው የሚያከናውኗቸውን ተግባራት በመከወን አቅማቸውን ሲያሳድጉና በማነኛውም የልማት እንቅስቃሴ ሲሳተፉና በተግባር ሲመዘኑ መሰረታዊ ትምህርት ያጠናቀቁ ያስብላቸዋል፡፡
የትምህርት ብርሃን ምዘናም ባለፉት ዓመታት በተለያየ መንገድ ማንበብ፣መፃፍና ማስላት ክህሉት ያዳበሩ ወጣቶችና ጎልማሶች ተገቢውን ምዘና እንዲያገኙ በማድረግና እውቅና በመስጠት ለቀጣይ ሀገራዊ ልማት ብቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል አላማ አድርጎ የሚሰጥ ምዘና መሆኑን አሰልጣኞች ተናግረዋል።
ምዘናውን ውጤታማ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባም አሰልጣኞቹ አክልው ገልፀዋል።
በስልጠናው የተሳተፉት ባለሙያዎች በበኩላቸው መንግስት አሁን ለጎልማሶች ትምህርት የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል። ባለፉት ዓመታት ጎልማሶትና ወጣቶች በዘርፉ መሰረታዊ ትምህርት ማግኘት አልቻሉም ተብሏል፡፡ በቀጣይም መንግስትና አጋር ድርጅቶች ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
በየደረጃው ያለው አመራርም ለዘርፉ ትኩረት ባለመስጠታቸውና በጀት ባለመመደባቸው ተጀምሮ የነበረው የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት መቆሙን የገለጹት ተሳታፊዎች በብዙ ወረዳዎች በየቀበሌው የተመደቡ አመቻቾችም መልቀቃቸው ለቀጣይ ስራችን እንቅፋት ስለሚሆን በየደረጃው የሚገኘው አመራር ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡
የትምህርት ብርሃን ምዘና አዲስ ፕሮግራም በመሆኑ ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ መፍጠር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ ምዘናው መጋቢት 29/2013 ዓ.ም ይሰጣል መባሉ በቂ ጊዜና በጀት ሳይኖረው መካሄዱ በስራቸው ላይ ጫና እንደሚፈጥርም ገልፀዋል፡፡
ምዘናው እንዲፈጥን የተደረገው በምዘናው የሚሳተፉ ጎልማሶችና ወጣቶች በቀጣይ ዓመት በሚጀመረው ሀገር አቀፍ የክህሎት ስልጠና እንዲሳተፉ ለማስቻል መሆኑንም የቢሮው አሰልጣኞች ተናግረዋል፡፡