የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ያዛጋጀው ክልላዊ የጥናትና ምርምር ሲፖዚየም ከሰሞኑ በባህርዳ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በጥናትና ምርምር ሲፖዜሙ በርካታ ትምህርት እና ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን የተናገሩት ተሳታፊዎች በተለይ ዳኞች የሰጡን አስተያየት ክፍተታችን እንድናይና በቀጣይ የተሻለ ጥናት እንድንሰራ አግዞናል ብለዋል፡፡ በየደረጃው ያለው የትምህርት መዋቅርና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም መምህራን ወደ ጥናትና ምርምር ገብተው የተማሪዎችን ውጤት እንዲያሻሽሉ ትኩረት አልሰጡትም ተብሏል፡፡ በየደረጃው የሚገኘው የትምህርት መዋቅር ለዘርፉ በጀት በመመደብና ስልጠና በመስጠት እንዲሁም ሲፖዜሞችን ማመቻቸት ይገባል ያሉት ተሳታፊዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ለመጀመሪያና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን በጥናትና ምርምር እንዲሳተፉ በመደገፍ ረገድ ያሳዩት ተነሳሽነት ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡
በበየምድር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህር የሆኑትና የጥናትና ምርምር ሲፖዜሙን ሲዳኙ ያገኘናቸው ረዳት ፕሮፌሰር አበበ ድግሴ በበኩላቸው የጥናትና ምርምሩን ስራ እንዴት ታዘቡት ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ የቀረቡ ጥናቶች እስካሁን ሲቀርቡ ከነበሩት በጥራትም የተሻሉ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡
መምህራን ተግባራዊ ምርምር ቢሰሩ ከዕለት ዕለት የመማር ማስተማር ሂደት የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል የምርምር አይነት በመሆኑ መምህራን እንዲሰሩ ይመክራሉ፡፡
በዚህ ሲምፖዜም የቀረቡ ብዙዎቹ ተግባራዊ ምርምሮች መምህራን የገጠማቸውን ችግር የፈቱበት ሂደት ነው ያቀረቡልን ብለዋል፡፡
አብዛኛው መምህራን ወደ ጥናትና ምርምር ስራ አለመግባታቸውን የተናገሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ የትምህርት ስራችን በጥናትና ምርምር እየፈታን ካልሄድን ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡መንግስትም ሆነ ሌላ አጋር አካላት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት መምህራን ወደ ጥናትና ምርምር ስራ እንዲገቡ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በሲፖዜሙ ማጠናቀቂያ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሴ አባተ የጥናት ውጤቶች በመማር ማስተማሩ ሂደት የሚገጥሙ ችግሮችን የሚፈቱ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ በየደረጃው የጥናትና ምርምር ስራዎች መጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ የተሻሉ የጥናት ውጤቶች ታትመው ለሌሎች መምህራን መማሪያ እንደሚሆኑም ተናግረዋል፡፡
በጥናትና ምርምር ሲምፐዜሙ 20 የጥናትና ምርምር ስራዎች የቀረቡ ሲሆን 10 የተግባር ምርምሮች ሲሆኑ 10ሮቹ ደግሞ መሰረታዊ ጥናቶች ናቸው፡፡
በክልላዊ ጥናትና ምርምር ሲምፖዜም አሸናፊ የሆኑ መምህራን የገንዘብና የሰርተፍኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡