የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለኦ ክፍል መምህራን ስልጠና ከሚሰጥባቸው የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች አንዱ የበጌምድር መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ነው።
በበጌምድር መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ የስልጠና አስተባባሪና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ባለሙያ አቶ አዳሙ ገ/ሕይወት ክልሉ ለኦ ክፍል መምህራን ተደጋጋሚ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አስታውሰው እሳቸው በሚያስተባብሩት ኮሌጅ በዚህ ዙር ብቻ 225 ሰልጣኞች እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደሳቸው ገለፃ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የ6 አመት ህፃናትን ቅድመ ቋንቋና ቅድመ ስሌት በማስተማር ለመደበኛ ትምህርት ለማዘጋጀት የሚሰጥ ስልጠና ነው።
በአጠቃላይ ስልጠናው መምህራኑ በስራ ቦታቸው ሲመለሱ ሊከውኗቸው የሚገቡ ተግባራትን እያከናወኑ፣ እርስ በእርስ እየተማማሩ፣ ተሞክሮዎችን እየተለዋወጡ የወሰዱት ስልጠና በመሆኑ አነቃቂና አይረሴ ነው ብለዋል።
አቶ የዋግነህ ቀለመወረቅ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የመምህራንና ትምህርት አመራር ልማት ቡድን መሪና ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን ለመጡ ሰልጣኞች አስተባባሪ ናቸው። አቶ የዋግነህ ስልጠናው በአፍ መፍቻ ቋንቋ እየተሰጠ መሆኑን ገልፀው መምህራኑ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ስልጠናውን መሳተፍ መቻላቸው ነገሮችን በቀላሉ እንዲረዱ ከማስቻሉም በላይ በስራ ቦታቸው ተማሪዎችን በቀላሉ ማስተማር እና ማስገንዘብ እንዲችሉ የሚረዳ ውጤታማ ስልጠና ነው ብለዋል።
አቶ ፈንታሁን ስዩም በዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ትምህርት መምሪያ የስርአተ ትምህርት ባለሙያና የስልጠናው ተሳታፊ ናቸው። በዚህ ስልጠና በመሳተፌ ለወደፊቱ መምህራንን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍና ክትትል ለመድረግ ያስችለኛል ብለዋል።
በአጠቃላይ ስልጠናው መምህራን እንዴት ማቀድ፣ እንዴት እና ምን ተጠቅመው ማስተማር፣ መመዘን፣ ድጋፎና ክትትል ማድረግ እና ግብረ መልስ መስጠት እንዳለባቸው የሚያሳይ ስልጠና ነው ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *