የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከዞንና የኮሌጅ አመራሮች፣ከመምህራንና ከተማሪዎላጅ ማህበር እንዲሁም ከወረዳ ትምህርት አመራሮችና ምዘናው ከተካሄደባቸው 71 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን ጋር ትናንት በደብረ ታቦር ከተማ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በዝቅተኛ የክፍል ደረጃ ከ1-4ኛ የክፍል ደረጃዎች ለሚገኙ ተማሪዎች በክልሉ በ71 ትምህርት ቤቶች ባለፈው ዓመት በሒሳብና በቋንቋ ትምህርቶች የተሰጠው ሳይሳዊ ምዘና አስተማሪ መሆኑ ተገልፃል፡፡
በውይይት መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) እንደተናገሩት በዝቅተኛው የክፍል ደረጃዎች የሚገኙ ተማሪዎች በመምህራን፣በወላጆችና በትምህርት አመራሩ የጋራ ትብብር አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ቢሆንም አብዛኛው ተማሪዎች ዝቅተኛውን የመማር ችሎታ አሟልተው ወደ ሚቀጥለው የክፍል ደረጃ እንዲዛወሩ ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ብርቱ ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የትምህርት ቤት አመራሮች የመማር ማስተማር ሂደቱን በቅርበት በመከታተልና በመደገፍ በተማሪዎችና በመምህራን መካከል ያለውን መስተጋብር የተሳለጠ እንዲሆን በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ያሉት ቢሮ ኃላፊው ከመምህራን ጥረት በተጨማሪ የወላጆች ክትትልና ድጋፍ ለተማሪዎች ውጤታማነት የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የተማሪዎችን የምዘና ስርዓት ሳይንሳዊ ማድረግና በአግባቡ እንዲመዘኑ በማድረግ ወደ ቀጣዩ ክፍል ማሸጋገር ይገባል፡፡ ተማሪዎች በክፍል ደረጃቸው ማወቅ የሚገባቸውን እውቀት ሳይጨብጡ ወደ ሚቀጥለው ክፍል ሊዛወሩ አይገባም ያሉት ቢሮ ኃላፊው ተማሪዎችን ማብቃት የሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካለት ሚና ሊታከልበት ይገባል ብለዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉት የትምህርት አመራሮች በበኩላቸው በውይይቱ ልምድ የተገኘበትና በቀጣይ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ለዝቅተኛ የክፍል ደረጃዎች የመሰረት የሆኑትን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ፕሮግራም ውጤታማ ለማድርግ የተጀመረውን አበረታች ስራ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
ተማሪዎች ውጤታማ ለማድረግ መምህራን ተማሪዎችን በደረጃ በመለየት አለመደገፍና የወላጅ ትምህርት ቤት ግኙኑነት ጠንካራ አለመሆን ለተማሪዎች አለመብቃት ምክኒያት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በየደረጃው ተመሳሳይ የውይይት መድረኮችን በማካሄድ የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል በትኩረት መስራት ይገባል ተብሏል፡፡