በምዕራብ ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ የሚገኘውና በ1941 ዓ.ም ስራ የጀመረው አንጋፋው የመራዊ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ ትላንት በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣አጋር አካላት፣የአካባቢው ማህበረሰብ፣የቀድሞው ተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል፡፡
ለረጅም ዓመታት ያገለገለውና በርካታ ምሁራንን ያፈራው የመራዊ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የመማሪያ ክፍሎች በማርጀታቸውና በመጎሳቆላቸው የመማር ማስተማሩ ስራ መታወኩ ያሳሰባቸው 10 ግለሰቦች እያንዳንዳቸው 50 ብር በማዋጣት ረጅም ራዕይ ሰንቀው ስራ ጀመሩ፡፡
ትምህርት ቤቱን ሙሉ በሙሉ በመቀየርና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማፍራት የተቋቋመው ኮሚቴ የአካባቢውን ማህበረሰብና የቀድሞው ተማሪዎች በማፈላለግ ስራ ጀመረ፡፡ ለዚህም የሚያግዘውን ሁነኛ አጋር ድርጅት ሲያፈላልግ በክልሉ ትምህርት ቤቶችን ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የሚገነባውና የመማር ማስተማሩን ስራ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚያግዘው ፓርተነርስ ኢን ኢዱክሽን ኢትዮጵያን በማግኘቱ ስራው በቅንጅት ተጀመረ፡፡
በ10 ግለሰቦች ጠንሳሽነት የተጀመረው ትምህርት ቤት በርካታ አካላት ተሳትፈውበት እንደተራራ የገዘፈው የመራዊ ትምህርት ቤት ችግር ተፈቶ 8 ብሎክ ያለው ደረጃውን የጠበቀ 24 የመማሪያ ክፍሎች፣ቤተመፀሀፍት፣ቤተሙከራና የአስተዳደር ህንፃ ተጠናቆ ለመመረቅ በቅቷለ፡፡
በምረቃ ፕሮግራሙ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ መኳንት አደመ የተጎሳቆለውን ትምህርት ቤት የአካባቢው ማህበረሰብ ከፓርተነርስ ኢን ኢዱክሽን ኢትዮጵያ እና ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር የተሰራውን ስራ አድንቀዋል፡፡ቀጣዩ ስራም ተማሪዎችን ውጤታማና ተወዳዳሪ ለማድረግ በግንባታው የተሳተፉ አካላት ሁሉ ከመምህራን ጎን በመሆን እንዲሰሩ አሳስበዋ፡፡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል እና የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ከህብረተሰቡና አጋር አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
የፓርተነርስ ኢን ኢዱክሽን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ይህአለም አበበ በግንባታ ሂደቱ የአካባቢው ማህበረሰብና ወጣቶች ህንፃው ዘመን ተሸጋሪ ይሆን ዘንድ በጥራት እንዲሰራ ሳይሰለቹ ያደረጉትን ክትትል አድንቀዋል፡፡
ይህን ህንፃ መገንባት ገንዘቡ ትልቅ ቢሆንም ስራው ግን ትንሽ ነው፡፡ ትልቁ ስራ ተማሪዎችን ውጤታማ ማድረጉ ላይ ነው የሚሉት ኃላፊው ተማሪዎች እንደ ትምህርት አቀባበላቸው ውጤታማ እንዲሆኑ መምህራን ተኪ የላቸውም ስለሆነም ድርጅታቸው የመማር ማስተማሩን ስራ እንደሚደግፍና ከመምህራን ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ በግንባታው የተሳተፉ አካላት በትልቁ ስራ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል፡፡ የመምህራንና የተማሪዎችን የአይን ምርመራና በማድረግ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግና ግቢውን አረንጓዴ የማድረግ ስራም የፕሮጀክቱ ሌላው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተስፋየ ሽፈራው ዩኒቨርሲቲው ከፓርተነርስ ኢን ኢዱክሽን ኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ የተናገሩት ም/ፕሬዘዳንቱ በግብአት ማሟላት፣ በጥናትና ምርምርና በስልጠና ስራዎች በመሳተፍ ትምህርት ቤቱን ሞዴል ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙ ተናግረዋል፡፡
የመራዊ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የቀድሞው ተማሪዎች በተወካዮቻቸው በኩል በትምህርት ቤቱና በአካባቢው ባሉ ሌሎች ትምህርት ቤቶች የሰሯቸውን ስራዎች ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይ ሊሰሩ ያቀዷቸውን ስራዎች ለህብረተሰቡ ይፋ አድርገዋል፡፡
የሌሎች ትምህርት ቤቶች የቀድሞው ተማሪዎችና የአካባቢው ተወላጆችም የተማሩበትን ትምህርት ቤት በመቀየር የመራዊን ተሞክሮ ሊወስዱ ይገባል መልዕክታችን ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *