19ኛው የአማራ ትምህርት ክልላዊ ልማት ትብብር (አትክልት) ፎረም በእንጅባራ ከተማ ትላንት የክልል የስራ ኃፊዎችና ዳይሬክተሮች፣የዞን ቡድን መሪዎች፣ በትምህርት ዘርፍ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡
ውይይቱን በይፋ የከፈቱት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ የክልሉ ትምህርት ውጤታማ ይሆን ዘንድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የመንግስትን ክፍተት በመሙላት ሰፊ ስራ መስራታቸውን ገልፀዋል፡፡ በተለይ የክልሉ ትምህርት በሰውሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የትምህርት ስራው ችግር ውስጥ ሲገባ ከመንግስት ጎን በመሆን ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በክልሉ ህፃናት ስም ድርጅቶችን አመስግነዋል፡፡
አሁንም የመማር ማስተማሩ ስራ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆኖ እየተካሄደ በመሆኑ ችግሮችን በመለየት ከመንግስት ጎን በመሆን ለችግሮች መፍትሄ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በውይይቱ የተለያዩ ሰነዶች የቀረቡ ሲሆን ዩኒሴፍ ትምህርትን በአደጋ ጊዜ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታና በአደጋ ምክኒያት ትምህርት እንዳይቋረጥ በሚደረጉ ጥንቃቄዎች ዙሪያ በቀረበው ጹሁፍ ውይይት ተደርጓል፡፡
የተመረጡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የአሰራር ተሞክሮዎችን በማቅረብ የተሞክሮ ልውውጥ ተካሂዷል፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸውን የትምህርት ስራዎችም ለአጋር አካላት አቅርቧል፡፡ የቢሮው የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መቅረቡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቀጣይ ስራ ለማቀድና ፕሮፖዛሎችን ለመቅረጽ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡
መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የመንግስትን ክፍተት የሚሞሉ በመሆናቸው ከትምህርት አመራሩና ባለሙያዎች ጋር በቅርበት መስራት ይገባል ተብሏል፡፡ መያዶች ችግር ለይተው የገቡ በመሆኑ ችግሩን የፈቱበት ሂደትና የመጣውን ለውጥ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
ማነኛውም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ስምምነት ሳይፈራረም በማነኛውም ስራ መሳተፍ እንደማይቻል የተገለጸ ሲሆን በዕምነት ተቋማት ላይ መሰረት አድርጎ ስራዎችን ማካሄድ እንደማይቻል በክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ በኩል ተገልጿል፡፡
መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚሰሯቸው መልካም ስራዎች ቢኖሩም ተሞክሮዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት የሌለ በመሆኑ በቀጣ ተሞክሮዎች የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ተደራሽ ማድረግ ይገባል ተብሏል፡፡
በአማራ ክልል በ2013 የትምህርት ዘመን በክልሉ ከ5መቶ ሚሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ በ50 መንግስታዊ ባለሆኑ ድርጅቶች 183 ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ ፕሮጀክቶች የክልሉን ትምህርት ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል፡፡
በቀጣይ ፎረሙ ለማጠናከርና የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ትምህርት ቢሮ፣አልማ፣ወርልድ ቪዥን፣ፓርትነርስ ኢን ኢዱኬሽን እና ፐላን ኢንተርናሽናል ፎረሙን እንዲያስተባብሩ በመምረጥ ፎረሙ ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *