የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2013 የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤቶች ያለውን የፈርኒቸር ችግር ለመፍታት የሚያስቸል ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡
በትምህርት ዘመኑ በጅኢኩፕ በጀት በ160 ሚሊየን ብር በመመደብ የተማሪ መቀመጫ ወንበሮችን እና የተለያዩ የመማር ማስተማር ስራዎችን የሚያግዙ የፈርኒቸር ግብአቶችን የማሟላት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ቢሮ የትምህርት ጥናት ግብአትና አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ይርሳው ብርሀኔ ተናግረዋል፡፡
ለሁሉም ዞኖች በጀቱን በመመደብ በኃላፊነት የሚከታተሉት የፈርኒቸር ግብአት ማሟላት ስራ በክልሉ የሚገኙ 117 ኢንተርፕራይዞች መሳተፋቸውም ታውቋል፡፡ኢንተርፕራይዞች በስራው መሳተፋቸው ለወጣቶች ስራ በመፍጠር በኩልም የራሱን ድርሻ የተወጣ ነው ተብሏል፡፡
ፈርኒቸሮቹ በጥራት እንዲሰሩ ክትትል እየተደረገ መሆኑንን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፈርኒቸሮች የተጠናቀቁ ሲሆን ቀሪዎቹ በበጀት አመቱ ማጠናቀቂያ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ገቢ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡