የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ባለፈው ሳምንት ዝውውርን አስመልክቶ በዚህ ገፅ ባወጣው መረጃ በርካታ መምህራን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
መምህራን ግልጽ ሊሆኑ ይገባሉ ያሏቸውን ጥያቄዎችንም በውስጥ መስመርና በአስተያየት መስጫ አሳውቀውናል፡፡ መምህራን ያነሷቸውን አስተያየቶች ቢሮው የተመለከታቸው ሲሆን ለቀጣይ ስራዎችም በግብአትነት እንደሚጠቀምበት እየገለፀ ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን የተወሰኑ ሃሳቦች ለክልሉ ትምህርት ቢሮና ለክልሉ መምህራን ማህበር ጥያቄዎች ቀርበው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በዚህ መሰረት በጉልህ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፡፡
1ኛ. በዝውውር ላይ የሀሰት ማስረጃ እንዴት ትከታተላላችሁ?
መምህራን ለዝውውር የሚያግዙና የተፈቀዱ የጋብቻ፣የህክምናና የማህበራዊ ጉዳይ ማስረጃዎች ከጤና ተቋም፣ ከፖሊስና ከፍትህ አካላት እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ቢሮው አጠራጣሪ የሆኑ ፊርማዎችንና ከተለያዩ ቦታዎች ጥቆማዎች ሲደርሱት ማስረጃውን ከሰጠው አካል የማረጋገጥ ስራ ይሰራል፡፡ በተለይ የሀሰት የህክምና ማስረጃ ከዚህ በፊት በተገኙ ጥቆማዎችና ፍተሻ ከጤና ተቋማት በማረጋገጥ የሃሰት ማስረጃ ሆነው በመገኘታቸው በህግ የተያዙ ጉዳዮችም እንዳሉም ታውቋል፡፡ ቢሮው ይህን አሰራር አጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በየደረጃው ለሚገኝ አካልም ጥቆማ በመስጠት መምህራን እንዲተባበሩ ተጠይቋል፡፡
2. በበረሃ አካባቢ ለሚሰሩ መምህራን መስፈርቱ በግልጽ አልተቀመጠም?
ለበረሃ እና ምቹ ለሆኑ አካባቢዎች መስፈርቱ ተመሳሳይ አለመሆኑን በዝውውር መመሪያው በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ምቹ መሰረተ ልማት ያለባቸው ወረዳዎችና መሰረተ ልማታቸው ባለመሟላቱ ለስራ ምቹ ያልሆኑ ቦታዎች የሚሰጣቸው የቦታ ነጥብ አንድ አይደለም ፡፡
ለአብነት ተመሳሳይ አገልግሎት ያላቸው ሁለት መምህራን በተለያየ ቦታ በመስራታቸው ለዝውውር የሚያዝላቸው አገልግሎት አንድ አይደለም ፡፡ አንድ መተማ ላይ የሰራ መምህር እና ጎንደር ከተማ ላይ የሰራ መምህር ወደ ባህርዳር ከተማ ለመዛወር ቢጠይቁ የሚሰጣቸው ነጥብ የተለያያ ነው ፡፡መተማ ላይ የሰራ መምህር አንድ አመት ወይም 12 ወር እንደ 17 ወር የሚያዝለት ሲሆን ጎንደር ላይ የሰራ መምህር አንድ አመት ወይም 12 ወር ምንም ጭማሪ ሳይኖረው በ12 ወር ብቻ ይታሰብለታል፡፡ሁለቱም መምህራን 10 ዓመት አገልግሎት ቢኖራቸው መተማ ላይ የሰራው መምህር ለሚሰራበት ቦታ በተሰጠው የቦታ ስሌት መሰረት አሰር አመቱ እንደ 14.16 ዓመት የሚያዝለት ሲሆን ጎንደር ከተማ የሰራው መምህር 10 አመቱ ተጨማሪ ሳይኖረው ለውድድር ይቀርባሉ ማለት ነው፡፡
3. በትምህርት ቤት ደረጃ የተሞላ ዝውውር በትክክል ወደ ክልል አይደርስም ለሚለው ጥያቄ?
በዝውውር መመሪያችን መምህራን በትክክል የዝውውር ቅጹ ትምህርት ቤት ላይ የሞሉ ከሆነና ለመሙላታቸውም በፊርማቸው ያረጋጡ ከሆነ በወረዳ ወይም በዞን ወይም በክልል ባለሙያዎች በሚፈጠር የመረጃ መዛባት መዛወር የሚገባው ቀርቶ ዝቅተኛ አገልግሎት ያለው ከተዛወረ ቅሬታ ቀርቦ በቅሬታ ወቅት እንዲስተካከል ይደረጋል፡፡ መምህሩም በትምህርት ቤትና በወረዳ ደረጃ የሞላው ዝውውር ስለሚለጠፍ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ የመምህራንን ዝውውር መረጃውን ያሳሳተው አካልም ተጠያቂ ይሆናል፡፡
4. በወረዳ ደረጃ ለሚሰራው ዝውውር ፍትሃዊ አደልም ለተባለው ጥያቄ?
በየደረጃው የሚሰራው ዝውውር ማስፈጸሚያ መመሪያ አንድ አይነት ነው፡፡ በወረዳ ደረጃ የሚሰራው ዝውውር የትምህርት ቤት ትምህርት ቤት በመሆኑ ለዝውውሩ ተዓማኒነትና ጥራት የወረዳው ሙያ ማህበር እና የወረዳው የትምህርት አመራር ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት ፡፡ የወረዳ መምህራን ልማት ባለሙያዎችና ሙያ ማህበሩ ጊዜ በመስጠት ጥራት ያለው ዝውውር የሚሰሩ ሲሆን ከዞንና ከክልልም ድጋፍና ክትትል የሚደረግ ይሆናል ፡፡
5. የክልል ክልል ዝውውር በተመለከተ?
የክልል ክልል ዝውውር የሚሰራው ከክልሎች በሚሰባሰብ መረጃ መሰረት በመሆኑ ከክልሎች በሚሰባሰብ የዝውውር ፍላጎት መሰረት በሃምሌ ወር ዝውውር ይፈጸማል፡፡
6. ቢሮው የሚያወጣቸው መመሪያዎች አለመሻሻልና ተደራሽ አለመሆን በሚል ለተነሳው ጥያቄ፡፡
በክልልና በፌደራል ደረጃ የሚወጡ መመሪያዎች በየጊዜው የሚሻሻሉና የተደራሽነት ለመቅረፍ በቢሮው ዌብ ሳይትና ቴሌግራም ገጽ መመልከት ይቻላል፡፡
የተከበራችሁ መምህራን ጥያቄዎች በከፊል ማብራሪያ የተሰጠባቸው እንህ ሲሆኑ በቀጣይ በሌሎቹ ጉዳዮች የምንመለስ ይሆናል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ2013 ትምህርት ዘመን የመምህራን ዝውውር የቅሬታ ምንጭ እንዳይሆን ጊዜ በመውሰድና በጥንቃቄ ሲሰራ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም እየተጠናቀቀ በመሆኑ በቀጣይ ሁለት ቀናት ውስጥ በዚህ ገፅ እና በሌሎቹ የቢሮው ማህበራዊ ገፆች የምናሳውቅ ይሆናል፡፡
ማሳሰቢያ ሁሉም መምህራን ሀሳቡን በመነፃነት ለማንሳትና ማብራሪያዎችን ለማግኘት ከቢሮው ጋር በቀጥታ ለመገናኘት የገፃችን ተከታይ ይሆን ዘንድ ሸር በማድረግና በማስተዋወቅ የበኩሎዎን ድርሻ እንዲወጡ በአክብሮት እንጠይቃልን፡፡ መልካም ጊዚ፡፡ መረጃ ሀብት ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *