===========================================================================
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች ባቋቋሙት የኤች አይ ቪ ኤድስ ፈንድ አማካኝነት ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ድጋፍ እየተደረገላት የተማረችዉ ተማሪ አበባ ጥላሁን በ2012/2013 የትምህርት ዘመን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስዳ 422 ዉጤት በማምጣት ወደ ዩኒቨሪሲቲ የሚያስገባ ውጤት አስመዝግባለች፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት አመራሮችና ሰራተኞች ለቀጣይ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷ የሚያስፈልጋትን የአልባሳትና የጽህፈት መሳሪያ ድጋፍ አድርገውላታል፡፡ ድጋፉ በተደረገበት ወቅት የተገኙት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሆኑት ፕሮፌሰር አለማየሁ ቢሻውና ዶክተር አስናቀው ታገለ ተማሪ አበባ ትምህርቷን ጠንክራ በመማር ለሌሎች ረዳት ለሌላቸው ህጻናት አርዓያ መሆን እንደምትችል ምክር ለግሰዋታል፡፡ በቀጣይም በገንዘብና በምክር ተማሪዋን ለማገዝ ቃል ገብተዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መኳንንት አደመ ተማሪዋ ትምህርቷን እስከምታጠናቅቅ ድረስ የቢሮው ሰራተኞችና አመራሮች እገዛና ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡
ተማሪ አበባ ጥላሁን በበኩሏ ለተደረገላት እገዛና ድጋፍ አመስግና ምንም እንኳን የተመደበችበት ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ከአካባቢዋ የራቀ ቢሆንም ጠንካራ በመማር ሃላፊነቷን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሰራተኞችና አመራሮች በየወሩ መዋጮ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የቢሮው ሰራተኞች የኤች አይ ቪና ኤድስ ፈንድ አራት ረዳት የሌላቸው ህጻናትን እየደገፈ በማስተማር ለይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *