የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ይልቃል ከፋለ /ዶክተር/ አዲሱ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ የመጽሃፍት ዝግጅት ከሰኔ 6 ጀምሮ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያው የሚካሄደዉ ከዚህ በፊት የነበረው ስርዓተ ትምህርት በባለሙያዎች ቡድን ጥናት ተደርጎበት በስነ ምግባሩ የታነጸና ችግር ፈች ትውልድ ለመፍጠር ሰፊ ችግሮች የነበሩበት መሆኑ በመረጋገጡ እንደሆነ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በሁሉም ባለድርሻ አካላትና ምክክር ከተደረገበትና ከተሳታፊዎች የተሰጡ ሃሳቦች በግብአትነት ከተካተቱበት በኋላ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በፍኖተ ካርታው ምክረ ሃሳብ መሰረትም የትምህርት ቤቶችን አደረጃጀት ማሻሻል፣ የመምህራንን የስልጠና ስርዓት መቀየርና የስርዓተ ትምህርት ለውጥ ማድረግ የሚጠበቁ ጉዳዮች እንድሆኑ ያሳያል፡፡
የትምህርት ቤቶች አደረጃጀት ወደ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ ደረጃ /ከ1ኛ_6ኛ ክፍል/፣ መለስተኛ ደረጃ / 7ኛና 8ኛ ክፍል/ ሁለተኛ ደረጃ /ከ9ኛ _12ኛ ክፍል/ ይለወጣል፡፡
የመምህራን ስልጠናን በተመለከተ የስልጠናው አይነትና ጊዜ ለውጥ ተድርጓል፡፡ በዚህም መምህራን ትምህርት ኮሌጆች የስርዓተ ትምህርት ረቂቅ ተዘጋጅቶ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ስነምግባር የተላበስ ሃገር ወዳድና ችግር ፈች ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል ስርዓተ ትምህርት ለማዘጋጀት ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከመምህራን ትምህርት ኮሌጆችና ከአንደኛ ደረጃ መምህራን እውቀት፣ ልምድ፣ ችሎታና ፍላጎት ያላቸው ሙሁራን መመረጣቸውን ቢሮ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
በሚቀጥለው አመት ጀምሮ በተመረጡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በመለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ሙሉ በሙሉ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት እንደሚተገበር ቢሮ ሃላፊዉ ተናግረዋል፡፡
የስርዓተ ትምህርት ዝግጅቱ በክልሉ የማስተማሪያ ቋንቋዎች አማርኛ፣ አዊኛ፣ ህምጣና እና ኦሮሞኛ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ሲሆን በአርጎብኛ ቋንቋም ስርዓተ ትምህርት ለማዘጋጀት ደግሞ ጥናት በመደረግ ላይ መሆኑንም ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት መሰጠት የሚቀጥል ሲሆን በሌሎች ቋንቋዎችም በክልሉ ትምህርት ለመስጠት በሙህራን ጥናት የተደረገ ይገኛል፡፡ የግዕዝ ቋንቋንም በክልሉ ለማስተማር ዝግጅት እየተደረገ እንድሚገኝና በተመረጡና ፍላጎት ባላቸው ትምህርት ቤቶች ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ቢሮ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ የመማሪያ መጽሃፍትንንና የተወሰኑ የመጀመሪያ ደረጃ መጽሃፍትን በኢ ፌ ዴ ሪ ትምህርት ሚኒስቴር እየተዘጋጁ መሆኑም ይታወቃል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሙያ ትምህርቶችን በመስጠት ተማሪዎች ትምህርታቸዉን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ስራ ለመሰማራት የሚያስችሉ የሙያ ችሎታና ክህሎቶችን የሚማሩበት ትምህርቶች ይካተታሉ፡፡
ተማሪዎች በሙዚቃ ስነ_ጽሁፍ፣ ቲያትር፣ ዳንስ፣ እንጨትና በረታ ብረት፣ ቆዳ ስራ፣ የሂሳብ አያያዝና የንግድ ክህሎት ሙያን እንዲጨብጡ የሚያስችሉ ትምህርቶች የሚሰጡ ይሆናል፡፡
በመሆኑም እነዚህን ትምህርቶች ለማስተማር በርካታ ግብዓቶችን የሚጠይቁ በመሆናቸው መንግስትና ኢንቨስተሮች ከፍተኛ ድርሻቸውን የሚወጡ እንደሚሆን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *