የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት አዲሱን የመማሪያና መስተማሪያ መፃህፍት ዝግጅት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በባህርዳር ከተማ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ በአማራ ክልል የምሁራን መማክርት ም/ቤት ፣በየደረጃው የሚገኙ በመፃህፍት ዝግጅቱ የሚሳተፉ የዩኒቨርሲቲ፣የኮሌጅና የመጀመሪያ ደረጃ፣ የሁለተኛ ደረጃ መምህራንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት አካሂዷል፡፡
በ1986 ዓ.ም የተቀረጸውና ለረጅም አመታት ሲያገለግል የቆየው የትምህርት ፖሊስ በበርካታ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ ሲያስነሳና ዜጎችን ሳያረካ ቆይቷል፡፡
ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ የሆነውን የትምህርት ስርአት ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥናት በሀገሪቱ ምሁራን ተዘጋጅቶ ሰፊ የህብረተሰብ ክፍል ዉይይት በማድረግ ግብዓት እንደሰጠበት ይታወሳል፡፡ በፍኖተ ካርታዉ ከተመላከቱ የመፍትሄ ሃሳቦች መካከል የስርዓት ትምህርት ማሻሻል አንዱ ነበር፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የመማሪያና ማስተማሪያ መፃህፍት ዝግጅት አጀማመር ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) እንደተናገሩት ትምህርት የሰው ልጅ የሚቀረጽበት መሳሪያ ነው፡፡ በሀገራችን ዘመናዊ ትምህርት ከተጀመረ ጀምሮ ባሳለፍናቸው መንግስታት የትምህርት ስራውን ውጤታማ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡
ካሳለፍናቸው የትምህርት ስርአቶች ለችግሮች መፍትሄ በማስቀመጥና ከጥንካሬዎች ትምህርት በመውሰድ የተሻለ ስርአተ ትምህርት መቅረጽ ይገባል ብለዋል፡፡
የትምህርት ስርአታችን በጥራት፣በተገቢነት፣በተደራሽነትና በፍታሀዊነት ህብረተሰቡን አለማርካቱንና ሀገሪቱ የምትፈልገውን የሰው ሃይልም ማፍራት አለመቻሉን የተናገሩት ቢሮ ኃላፊው አዲሱ ስርአተ ትምህርት ያለፉትን ችግሮች የሚፈታና በቀጣይ በስነ- ምግባሩ፣በአመለካከቱና በክህሎቱ የዳበረና ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለመፍጠር ወጥ በሆነ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ያአማራ ክልል ምሁራን መማክርት ምክር ቤት የዚህን ታሪካዊ ኃላፊነት ወስዶ ወደ ዝግጅት መግባቱን የገለጹት ቢሮ ኃላፊው ማንኛውንም መስዋትነት በመክፈል ታሪክ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የምሁራን መማክርት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ዶክተር ገበያው ጥሩነህ በበኩላቸው ም/ቤቱ ይህን እድል በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ትውልድን የሚያሻግር መፃህፍት ለማዘጋጀት ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡
የሚዘጋጀው ስርአተ ትምህርት አመለካከታትን የሚቀይር መሆን አለመበት የሚሉት ዶ/ር ገበያው ትውልድን ለመገንባት የሚሰራ በመሆኑ ምክርቤቱ ትልቅ ዋጋ በመስጥ ይመለከተዋል ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሰት የሰጠንን አደራ ተቀብለን በውጤታማነት በመስራት ችግር ፈች ትውልድ በመፍጠር የዚህን ታሪካዊ አደራ እንደሚወጣ አክለው ገልፀዋል፡፡
መርሃ ግብሩን በይፋ የከፈቱት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) ባለፈው ስርአተ ትምህርት ስንቆጭበትና ስናለቅስ የቆየንበት ጉዳይ አሁን በእኛ እጅ ውስጥ ሆኗል፡፡ የዚህን ታሪካዊ አደራ የተቀበልን ሰዎች የነበረውን የስርአተ ትምህርት ጉድለት በመለየት እንደ አማራ ክልል የጎደሉ ይዘቶችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሄ ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል፡፡
የትምህርት ስርአታችን ዋናው ስብራት የአገር በቀል እውቀትን አለመጠቀም በመሆኑ ይህን በማድረግ ታላቅነታችን መመለስ ይገባል ያሉት ኃላፊዋ ለዚህ ታላቅ ተግባር እውቀታችሁንና ልባችሁን በመስጠት በታሪክ አጋጣሚ ያገኛችሁትን አደራ በድል በመወጣት ታሪክ እንዲዘክራችሁ ስሩ ሲሉ ከአደራ ጋር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የክልሉ መንግስትም ለዚህ ታላቅ ተግባር በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
መርሃ ግብሩ ከሰኔ6 -10/2013 ዓ.ም እንደሚቆይ ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *