የግዕዝ ቋንቋን በመደበኛው ትምህርት ውስጥ እንደ አንድ የትምህርት አይነት በቀጣዩ የትምህርት ዘመን በተመረጡ ትምህርት ቤቶች መስጠት እንደሚጀመር የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ግዕዝን በመደበኛ ትምህርትነት ለማስጀመር የሚያስችል የውይይት መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያን የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ለማወቅና ሀገር በቀል እውቀቶችን በአግባቡ ተጠቅሞ ሀገራዊ እድገት ለማረጋገጥ የግዕዝ ቋንቋ በትውልዱ በስፋት እንዲታወቅ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ግዕዝን ከእኛ ከባለቤቶቹ ይልቅ የተለያዩ የውጭ ሀገራት እስከ 3ኛ ዲግሪ ድረስ በማስተማር በአግባቡ አጥንተው ተገልግለውበታል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ብዙዎቹ ቀደምት መፅሐፍት በግዕዝ የተፃፉ እንደመሆናቸው ቋንቋውን ማወቅ የኢትዮጵያን የቆየ ጥበብ ለመጠቀም ያስችላልም ብለዋል።
ወደፊትም ከግዕዝ በተጨማሪ የአረብኛ ቋንቋን በጥናት ላይ ተመስርቶ በተመረጡ የክፍል ደረጃዎች እንዲሰጥ ይደረጋልም ተብሏል።
ይህም ብዝሀ ልሳን የሆነ ማህበረሰብ በመፍጠር በየትኛውም አካባቢ ተግባብቶ ለመስራትና ለመኖር እገዛው የጎላ መሆኑ ተገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *