ሰኔ 9/2013 ዓ.ም
ባህርዳር
የግዕዝ ትምህርትን በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ለመስጠት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ የግዕዝ ቋንቋን እንደ አንድ የትምህርት አይነት በመደበኛው ትምህርት ቤት ለመስጠት የሚያስችል ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በባህርዳር ከተማ አካሂዷል፡፡
በምክክር መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) የጥንታዊ ስልጣኔ ሚስጢር ዋናው ምኪኒያት የግዕዝ ትምህርት ነው፡፡ አሁን ለደረስነበት የስልጣኔ ዘመንም ዋናው መነሻ ግዕዝ መሆኑን የተናገሩት ቢሮ ኃላፊው መንፈሳዊና ጥበባዊ መፃህፍት የተፃፉበት ቋንቋ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ቀደምት ሊቃውንት በብዙ ደክመውበት ያበለፀጉትን ሀብት አለመጠቀማችን ሊያስቆጨን ይገባል፡፡አሁን ያለንበነት ጊዜ የአገር በቀል ዕውቀትን ለመጠቀም የሚያስችል ምቹ ጊዜ በመሆኑ የግዕዝ ቋንቋን እንደ አንድ የትምህርት አይነት በመደበኛ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ምቹ ጊዜ ነው፡፡
ቋንቋን መማር ዘርና ሀይማኖት አይለይም የሚሉት ኃላፊው የተጀመረው ስራ ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የጎላ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ ትምህርት ክፍል ምሁራን ባቀረቡት መነሻ ጹሁፍ ሰፊ ውይይትና ክርክር የተካሄደ ሲሆን በቀጣይ አመት ትምህርቱን ለማስጀመር የሚያስችል የስርአተ ትምህርት ቀረፃ፣መምህራንን የማዘጋጀት፣ በየትኛው የክፍል ደረጃ ሊሰጥ ይገባል በሚሉና በሌሎች ጉዳዮች ምክክር ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ ፕ/ር ዓቢይ ግዛው የግዕዝ ቋንቋ ትንሳኤ የአገር በቀል እውቀት ትንሳኤም ነው ብለዋል፡፡ ግዕዝ ሀገሩ ከዚህ ሆኖ በተለያዩ አለማት የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እስከ ፒኤችዲ ዲግሪ ድረስ ማስተማራቸው ሚስጥሩ ስለገባቸው ነው፡፡ የኛን ጥበብ ወደዱት የጥበቡ መገለጫ ደግሞ ግዕዝ መሆኑ በማወቃቸው ለዘርፉ ትኩረት መስጠታቸውን ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል፡፡
በቀጣይ የትምህርት ዘመን የግዕዝ ትምህርትን በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅትም ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ከሀይማኖት አባቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበትና በቅንጅት ለመስራት ስምምነት ተደርሷል፡፡
የግዝ ትምህርትን ውጤታማ በማድረግ በስነምግባሩና በዕውቀቱ የላቀ ጠበብት ትውልድ ለማፍራት የተጀመረው ስራ ውጤታማ ይሆን ዘንድ የዘርፉ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት በመተባበር ታሪካዊ ሀላፊነታችን ልንወጣ ይገባል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ Amhara National Regional State Education Bureau
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse
ፌስቡክ https: Amhara Education Bureau