አገራችን ኢትዮጵያ የጥበበኞችና የአዋቂዎች አገር ናት፡፡ አገራችን፤
• የራሷ ፍልስፍና፣
• በህክምናው ዘርፍ ምጡቅ እውቀትና የመድሃኒት ቅመማ ክህሎት፣
• በፍካሬ ከዋክብት፣
• በኪነ-ጥበብ፣
• በታሪክ፤
• በሥነ-ጽሑፍ፣ ከፊደል ጀምሮ፣
• በግብርና እውቀት፣ በሌሎችም ጉዳዮች፤ ያላት ሀገር ናት፡፡
በአገርኛ እውቀት (indigenous knowledge) የበለፀገች፣ ወደር የማይገኝላት ሀገር ናት፡፡
ይህ ሁሉ ሀብቷ ተመዝግቦ የሚገኜው በጥንቱ ቋንቋዋ በግዕዝ ነው፡፡
ግዕዝን ብዙ ሀገሮች የራሳቸው ለማድረግ ተመኝተውታል፤ ይመኙታልም፡፡ ግን አልታደሉትም ነበርና ባልተረዳነው ባልገመትነው መንገድ የራሳቸው አድርገውታል፡፡
ዛሬ በዓለም በርካታ አገሮች በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ እያስተማሩት ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ጀርመን፣ አሜሪካና ሌሎችም በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡
ለምን?
• ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የጥበበኞች፣ የባለአእምሮ አባቶቻችን ያወቋቸው እውቀቶችም ጥበቦችም ለእኛ ትውልድ እንዲደርስ በቋሚነት የመዘገቧቸው በግዕዝ ቋንቋ በመሆኑ፤
• በዚህ ምክንያትም ባዕዳን ጥበቦቻችን ወደዷቸው፤ ሊያገኙዋቸው የሚችሉትም ግዕዝን ሲያውቁ በመሆኑ፤
• ስለዚህ በግዕዝ የተጻፉ መጻሕፍቶቻችን በተለያዬ መንገድ ተወሰዱ፤ ተዘረፉ፤ እኛም በዘረፋው አገዝናቸው ከሁለት በአንዱ ምክንያት፤ ባለማወቅ ወይም በጥቅም ፈላጊነት፡፡
• መዛግብቱን የፈለጉበት ምክንያት በመጻሕፍቱ ውስጥ ያሉትን ጥልቅና ምጡቅ እዉቀቶች ለማወቅና ለመጠቀም ግዕዝን ማወቅ ስላስፈለጋቸው ነው፡፡
እኛስ?
• ቋንቋ ከማናቸውም ነገር ጋር ተፈጥሯዊ ቁርኝት እንደሌለው እየታወቀ ከሃይማኖት ጋር ስላስተሳሰርነው፤
• የሀገራችን ሀብት ንቀን የውጩን ለመቃረም ፍላጎታችን በመናሩ፣ የራሳችን የሆነውን በመጥላታችን ወይም በመናቃችን፤ ግን እንደሚታወቀው ብዙ የሥነ-ጽሑፍ ሀብት አለው የተባለው አማርኛ ቋንቋ እንኳ “ካለግዕዝ እገዛ አይሆንልኝም” እያለ፤
 ይህን ሀብቱን ወደን የጠላነው፣
 እየተበደርነው ያላመሰግንነው፣
 ከተፈጥሮ ግብሩ ይልቅ ባልዋለበት ያቆራኜነው፣
 የጣልነው፣ ያጣጣልነው፣
 ወለላውን (የግዕዝን ማር) እኛን መግለጽ ባጠጠን ቁጥር የምንልሰው፣
 ግን ለማወቅም ለማሳወቅም የማይዳዳን፣
 የእሱን ሀብት እንደራሳችን ወስደን እየተጠቀምን ግን ውለታውን የረሳነው፣
 ሀብቱ ግን ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም ከነገ ወዲያም የሚጋጥ፣ የማይነጥፍ የማይጎድለው፣
 እምቢ አንሻህም ቢባል እንኳ ጎምርቶ፣ ጎልብቶ የሚታየው ቋንቋ ግዕዝ ነው፡፡
እንረዳው፤
• የግዕዝ ቋንቋ ለምናቀነቅንለት ለዘመናዊ ትምህርት ከምናስበው በላይ ጠቃሚ ነው፣
• የቅኔ ትምህርት የማስተማሪያ ዘዴ፣ ፈጠራን የማዳበር ስልቱ፣ የማስቻያው መንገድ፣ አቀኛኜት በዓለም የሌለ የእኛ የኢትዮጵያውያን ልዩ ችሎታ ነው፤
• ከፊደል እስከ ላይኞቹ የትምህርት ውቅሮች ግዕዝ የሚሰጥበት የትምህርት ዘዴ ለዘመናዊ ትምህርት ብንጠቀምበት፤
 በፈጠራ ችሎት ማዳበርን
 ጥልቅ እውቀትን ማዳበርን
 ተመራማሪነትንና
 በራስ መማርን፤ ያዳብራል፡፡
• አንድ መምህር በርካታ ተማሪዎችን በብቃት ሲያስተምር፤
• በ EGRA ጥናት እንደታየው ተማሪዎቻችን 4 ዓመታት ድረስ እንኳ ተምረው ፊደል መቁጠር ያልቻሉ መሆኑ ሲታይና በግዕዝ ጅማሬ ትምህርት በአጭር ጊዜ ፊደል መቁጠር፣ ንባብ መጀመር ሲታይ ዛሬ በቁም ነገር ስለግዕዝ በትምህርት ቤቶች ማስተማር የተጨዋወትነው ጉዳይ የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ይታየኛል፡፡
እንረዳው፤
• የግዕዝ ሀገሩ ከዚህ ከኢትዮጵያ ነው፣
• በቋንቋነት ተፈጥሮው አቅፎ የያዘውን መንፈሳዊና ለሰው ልጅ ጠቃሚ የሆኑ ሌሎች እምቅ ሀብቶቹን፤ ከአድማስ ባሻገር ስላለው እውቀትና እውነትንም እንድንማር ባዕዳን ቋንቋውን እያጠኑ ስለመሆናቸው ከማድነቅ አልፈን የእኛ ነህ ልንለው ይገባል፡፡
በዚህ ረገድ የዛሬው ጅማሮ ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡
ዛሬ፤
• ጥሩ ነገር ይታየኛል፤ ወደ አገርኛው እውቀት እንመለስ የሚል፡፡
• የግዕዝ ትንሣኤ ለአገርኛው እውቀት ማደግ የላቀ ጠቀሜታ አለው፡፡
ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ለማስተማር ስናስብ፤
• የመምህራን ሥልጠናው ላይ፣
• ካሪኩለም ቀረጻው ላይ፣
• መጻሕፍት ዝግጅቱ ላይ፣ ልናተኩር ይገባል፡፡ ካለ እነዚህ ጉዳዮች ስኬት ሊኖር ስለማይችል፡፡
ግን፤
• የዋቆ ሀሳብ (ከሁኔታዎች ጋር አስማምቶ እርምጃ መውሰድን) መተግበር እንዳለበት ይታየኛል፤ ግዕዝ አዋቂዎችን በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ላይ ቢሆኑም በአስተማሪነት፣ ቢያንስ በአጋዥነት ማሳተፍ ግዴታ ይመስለኛል፤ ባይሆን እስከጊዜው ድረስ (በግዕዝ ቋንቋ ምሩቃን መምህራንን እስክናገኝ)፡፡
• የግዕዝ ትምህርት በታለመለት ጊዜ እንዲጀምር የሁላችንም ርብርብ ያስፈልጋልና በትጋት እንሥራ እላለሁ፡፡
በመጨረሻም ምሥጋና፤
ይህን ሃሳብ ያፈለቁ ሰዎችን እጅግ አድርጌ አመሰጋናለሁ፡፡ ከሁሉ በፊት ግን ጽንሱን ከአምስት ስድስት ዓመት በፊት ለአማራ ዩኒቨረሲቲዎች ፎረም ግዕዝን ማስተማር ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ብንጀምርስ በሚል ሃሳብ አቅርበው የነበሩትን አቶ ይትባረክ ደምለውን ለዚህ ጽንስ አስተዋፅዖ ስለማድረጋቸው ሁሌም ልንዘክራቸው የተገባ ሲሆን ምሥጋናም ይገባቸዋል፡፡ አሁን ደግሞ ተግባራዊ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ላደረጋችሁ ወንድሞቻችን እግዚአብሔር ዋጋውን ይክፈላችሁ፡፡ ከሁሉ በላይ የክልሉን የትምህርት ቢሮ በአጠቃላይ; የቢሮውን ኃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለን በተለይ; ስላላቸው ስለአገራዊ እውቀት ብልፅግና መልካም ፈቃድና ኢላማ እጅግ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ በተለይም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኜና የአካዳሚክ ም/ ፕሬዚደንተ ዶ/ር እሰይ የግዕዝ ትምህርት ተግባራዊ እንዲሆን ላደረጉት አስተዋፅኦ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ሌላው ሳላመሰግን የማላልፈው በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሂውማኒቲስ ፋኩልቴ የሚገኙትን የግዕዝ ትምህርት ክፍል መምህራንና የፋኩልቴው ዲን የነበሩት ዶ/ር ዳዊት አሞኜን ነው፡፡ ዶ/ር ዳዊት አሞኜ ይህን የተቀደሰ ዓላማ በፋኩልቴው በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ እንዲጀመርና እንዲጎለብት ከማድረጋቸው ባሻገር ዛሬ በትምህርት ቤቶች ደረጃ (ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ) እንዲሰጥ መሠረት ከጣሉት ውስጥ አንዱና ዋነኛው መሆናቸውን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ የግዕዝን ጉዳይ ጉዳዬ ነው ብላችሁ ጊዜያችሁን በመሰዋት እዚህ ለተሰበሰባችሁና ለተወያያችሁ፣ ለታላቁ ዓላማ መሳካት አስተዋፅኦ ላደረጋችሁ፤ ለሁላችሁም፣ እግዚአብሔር ክብር ይስጥልን፡፡ መልካምን ሁሉ ያጎናፅፍልን፡፡
በመጨረሻም፤
የሀገራችንን ሀብት ግዕዝን አውቀን፤
በቋንቋው ተሰንዶ ያለውን፣ የታመቀውን እውቀት ቀስመን፤
በተለያዩ ዘርፎች ሀገራዊ እውቀቶችን ገብይተን፤
ለትውልድ አስተላለፈን፤
ለሀገራችን እድገትና ብልጽግና አስተዋፅኦ እናድርግ፡፡
እንሰማማ፤
እውቀት ከውጭ ሲመጣ ብቻ ጀሯችን ቀና ማድረጉን በገደብ እናድርገው፡፡ አዎ ጠቃሚ የሆኑትን ከሌሎችም አንወስድም ማለት ግን አይደለም፡፡ መገንዘብ ያለብን ከእኛም ቤት እውቀትም ጥበብም አለ፤ የእኛ የሆነ፡፡
ምሥጋና ለአባቶቻችን ይሁን!!!
እውቁ ምሁር ፕሮፌሰር አብይ ግዛው የግእዝ ቋንቋ በትምህርት ቤቶች ለማስተማር ከምሁራንና ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው የምክክር መድረክ ላይ ያደረጉት የመዝጊያ ንግግር፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ Amhara National Regional State Education Bureau
በቴሌግራም https://t.me/anrse
ፌስቡክ https: Amhara Education Bureau

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *