የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለመምህራን ትምህርት ኮሌጆች፣ ለዞንና ወረዳዎች ኤች አይ ቪና ስርዓተ ጾታ ፎካሎች ኤች አይ ቪ /ኤድስ/ና ስርዓተ ጾታ በስራ ማካተት፣ በትምህርት ቤትና አካባቢዎች የሚከሰቱ ጾታዊ ጥቃቶችን መከላከል ላይ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
======================================
ስልጠናውን የሰጡት በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ጾታና ኤች አይ ቪ/ ኤድስ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት አቶ ፈንታሁን ተሰጋ እየተዘነጋ የመጣውን የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና በስርዓተ ጾታ ጉዳዮችን ላይ ለውጥ ለማምጣት በትምህርት ዘርፉ እቅድ ላይ በማካተት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በስልጠናው ላይ ተሳታፊ የነበሩት የፍኖተ ሰላም መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ ስራነህ ተጫነ ኮሌጃቸው በስርዓተ ጾታና ኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ የኮሌጁ ማህበረሰብ ያለበትን የግንዛቤ ደረጃ በጥናትና ምርምር በመለየት ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ስራዎችን የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሴት ተማሪዎች በመምህራኖቻቸውና በሌሎች አካላት ተጽዕኖ እንዳይደርስባቸው እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ስራነህ ለ25 ችግረኛ ተማሪዎችን የፍኖተ ሰላም መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ነጻ የትምህርት እድል ሰጥቶ በማስተማር ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም በኮሌጁ አመታዊ እቅድ ላይ ኤች አይ ቪ ኤድስንና ስርዓተ ጾታን በማካተት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው የስልጠና ተሳታፊ የወልድያ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ ሰለሞን ካሳዬ በስልጠናው በርካታ ጉዳዮችን እንደተረዱ ተናግረዋል፡፡ የወልድያ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የስርዓተ ጾታና ኤች አይ ቪ ኤድስ ክበባትን በማደራጀትና በመደገፍ ለተማሪዎች ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ለተማሪዎች በተፈጠራላቸው ግንዛቤ ራሳቸውን ከኤች አይ ቪ /ኤድስና ጾታዊ ጥቃት አስቀድመው እንዲከላከሉ ማስቻሉን ተናገረዋል፡፡ የወልድያ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ከአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን ለሴት ተማሪወች ጥያቄና መልስ ውድድሮችን በማዘጋጀትና ለአሸናፊዎች ሽልማትና እውቅና በመስጠት እያበረታታ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ኮሌጁ ችግረኛ ተማሪዎችን በነጻ ማስተማር እንዲሁም ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው ያለባቸውን ተማሪዎች በኢኮኖሚ እየደገፈ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ተማሪዎችና የኮሌጁ ማህበረሰብ የባህሪ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ግንዛቤዎችን በመፍጠር ከኤች አይ ቪ ኤድስ ራሳቸውን የጠበቁ፣ በጾታ እኩልነት የሚያምኑ፣ በሙያቸው የተካኑ መምህራን ለማፍራት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ Amhara National Regional State Education Bureau
በቴሌግራም https://t.me/anrse
ፌስቡክ https: Amhara Education Bureau

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *