በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጎንደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሰራተኞች ለፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታ የሚውል የ724ሽ 570 ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡
በጎንደር ከተማ የሚገኘው አንጋፋው የፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 1934 ዓ.ም የተመሰረቶ በርካታ ምሁራንን አፍርቷል፡፡የትምህርት ቤቱን ደረጃ ለማሳደግና የማስፋፊያ ግንባታ ለማከናወን የ70 ሚሊየን ብር ፕሮጀከት ተቀርፆ እየተራ መሆኑን የትምህርት ቤቱ ማስፋፊያ ግንባታ ኮሜቴ አባል አቶ ወልዴ መና ተናግረዋል፡፡በትምህርት ቤቱ በህብረተሰቡ ድጋፍ እየተገነባ የሚገኘው ባለ 30 መማሪያ ክፍሎች ፣ባለ አራት የላብራቶሪና አንድ የላይብረሪ ከፍሎች ያሉት ባለ ሁለት ወለል ግንባታ ከጥር 2012 ጀምሮ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ እስካሁንም የግንባታው 50 በመቶ መድረሱንም ገልፀዋል፡፡ እስካሁንም ከተለያዩ አጋር አካላት 12 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉን አቶ ወልዴ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጎንደር ቅርንጫ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደሞዜ ባይቤ ደግሞ የተቋሙ ሰራተኞች 820ሽ ብር ለትምህርት ቤቱ ድጋፍ ለመስት ቃል የገቡ ሲሆን በዛሬው እለትም ከተቋሙ ሰራተኞች በጥሪ ገንዘብ የተሰበሰበውን የ724ሽ 570 ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
የተሰበሰበውን የገንዘብ ድጋፍም ደረሰኝም ለጎንደር ለከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ አስረክበዋል፡፡ከንቲባው በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለፁት ከተደቀነብን ህልውና ዘመቻ ጎን ጎን ልማቱንም አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አልማ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አደራጀው አላበ ደግሞ ህብረተሰቡ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግ እያበረከተ ያለው ድጋፍ ከጊዜ ጊዜ እድገት እያሳየ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ወንድማኝ ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግ ህብረተቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *