ዶክተር ይልቃል ከፋለ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮን መምራት ከጀመሩበት ህዳር 2009 ዓ.ም ጀምሮ በቅንነትና ውጤታማ በሆነ አመራር ሰጭነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮን በሃላፊነት ሲመሩ በቆዩባቸው አመታት በክልሉ ትምህርት ላይ በርካታ ውጤታማ ተግባራት አከናውነዋል፡፡
የህወሃት መራሹ መንግስት በክልላችን ያሉ ህጻናትን በዳስ እንዲማሩና የአማራ ክልል ህዝብ ልጆች እንዳይማሩ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ዶክተር ይልቃል ከፋለ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሆነው ከተሾሙ በኋላ የክልሉ ትምህርት ቤቶች ከዳስ ወደ ክላስ ለመቀየር በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡ በዚህም ከክልሉ ባለሃብቶች፣ በውጭ ከሚገኙ የክልሉ ተወላጆች፣ ከድርጅቶችና መላው ትምህርት ደጋፊ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር በርካታ ትምህርት ቤቶችን ከዳስ ወደ ክላስ እንዲቀየሩ ሰርተዋል፡፡
የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ ጋር በመተባበርና በመቀናጀት መላው የክልላችን ህዝቦች፣ የዲያስፖራ አባላትና ባለሃብቶች የሚራባረቡበት የክልሉን ትምህርት ቤቶች ገጽታ ለመቀየርና ደረጃ ለማሻሻል በቦርድ አመራርነት አገልግለዋል፡፡
ለአማራ ክልል ህጻናት መማር ሌት ተቀን የታተሩት ዶክተር ይልቃል ከፋለ የክልሉ መምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ብርቱ ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህም በርካታ መምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ በነጻ እንዲያገኙ አስችለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መምህራን የሙያዊ ክህሎታቸውን እንዲያሻሽሉና የትምህርት ደረጃቸውን እንዲያሳድጉ ጥረት አድረገዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት እንቅስቃሴ ላይ አወንታዊ አሻራቸውን ያሳረፉት ዶክተር ይልቃል ከፋለ ካሁን በፊት የነበረው የትምህርት ፖሊሲ ለሀገራችን ብሎም በክልላችን ያመጣዉን አሉታዊ ተጽዕኖ በመረዳት እንዲቀየር የመፍትሄ ሃሳቦችን ለሚመለከተው አካል ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በዚህም ፖሊሲው የነበረበት ክፍተት በሙሁራን ተጠንቶ ችግሮች ተለይተዋል፡፡ አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀቶ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በመሆኑም በክልላችን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት እንዲከናወን አድርገዋል፡፡
በመጽሃፍ ዝግጅቱን የአማራ ሙሁራን መማክርት ጉባኤ በበላይነት እንዲመራና እንዲያስተባብር በመስጠት የመጽሃፍት ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፡፡
በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ለሃገር በቀል እውቀት ትኩረት እንዲሰጥ ፣ ስነ ምግባር የተላበስ ፣ ስራ ፈጣሪ፣ ሃገሩን ወዳድ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት አድርጎ እንዲቀረጽ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሰርተዋል፡፡
በርካታ እምቅ ሃብቶች ያሉት የሳይንስና ጥበብ መነሻ የሆነውን የግእዝ ቋንቋን በክልላችን በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለማስተማር ስርዓተ ትምህርት እንዲቀረጽ አድርገዋል፡፡ በቀጣይም የአረብኛ ቋንቋን ጨምሮ ሌሎች ቋንቋዎችን ለክልሉ ህጻናት ለማስተማር ከባለድርሻ አካላትና ምሁራን ጋር ምክክርና ጥናት እንዲደረግ አመራር ሰጥተዋል፡፡
በክልላችን የሚገኙ የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች የተጣለባቸውን መማር ማስተማር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና ጥናትና ምርምር ተግባራትን እንዲወጡ አመራር በመስጠትና በመደገፍ በትጋት ሰርተዋል፡፡
ዶክተር ይልቃል ከፋለ በክልላችን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የነበረባቸውን የተማሪዎች መቀመጫ ወንበር ችግር ለመቅረፍ ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ ከ አንድ መቶ ሽህ በላይ የተማሪዎች መቀመጫ ዴስክ ወንበሮችን ተሰርተው እንዲሰራጩ አድርገዋል፡፡
ከዚህ በፊት በክልላችን ያለነበረውን አዳሪ ትምህርት ቤት ችግር ለመቅረፍ በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡ በጅምር ላይ የነበረውን የደሴ አዳሪ ትምህርት ቤት ስራ ለማስጀመር አመራር ሰጥተዋል በዚህም የደሴ አዳሪ ትምህርት ቤት ከ300 በላይ ለክልላችን ብሎም ለሃገራችን የነገ ተስፋ የሚሆኑ ልዩ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ ሌሎች አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በባህር ዳርና ጎንደር ለማስገንባት ጥረቶችን አድርገዋል፡፡
ከዚህ በፊት በክልሉ የትምህርት ስርዓት የነበሩና ለስራ አስቸጋሪ የሆኑ በርካታ መመሪያዎች እንዲሻሻሉ አመራር ሰጥተዋል፡፡
ክልላችን በኮቪድ፣ በአንበጣ ወረርሽኝና በግጭቶች በተፈተነበት ሰዓት በክልላችን ለሚገኙ የትምህርት አመራሮች በቀውስ ወቅት በክልሉ ትምህርት ለማስቀጠል የሚያስችልና አቅም የሚያጎለብቱ በርካታ ስልጠናዎችን እያዘጋጁ አሰልጥነዋል፡፡
ዶክተር ይልቃል ከፋለ የቢሮአችን ሃላፊ ሆነው ባገለገሉበት ያለፉት አምስት አመታት ሁሉ በትምህርት ዘርፉ አመራሮችና ሰራተኞች ዘንድ ተወዳጅ፣ ቅን፣ ግልጽ፣ ተጋባቢና በሳል አመራር የሰጡ ናቸው፡፡
ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጀግና፣ ኩሩና አስተዋይውን የአማራ ክልል ህዝብ ለመምራት በአማራ ክልል ምክር ቤት ዛሬ መስከረም 20/2014 ዓ.ም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ስለተሾሙ እንኳን ደስ አለዎት እያልን ቀጣዩ የስራ ዘመንዎት ስኬታማና ውጤታማ እንዲሆን እንመኛለን፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ Amhara National Regional State Education Bureau
በቴሌግራም https://t.me/anrse
ፌስቡክ https: Amhara Education Bureau

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *