የአሸባሪዉ ህውሃት ቡድን ወረራ ጉዳት ባደረሰባቸው አካባቢዎች የሚያስተምሩ መምህራን ተማሪዎችንና ህብረተሰቡን ከደረሰበት ሃዘን፣ ቁዘማና ድባቴ በማውጣት ዉጤታማ የመማር ማስተማር ስራ ለማከናወን ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ፡፡
——————————————————–
በደቡብ ጎንደር ዞን አሸባሪው የህውሃት ቡድን ወረራ ፈጽሞ ጉዳት ባደረሰባቸው ወረዳዎች ለሚያስተምሩ መምህራን የስነ ልቦና ግንባታ ስልጠና በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ነው፡፡
ስልጠናው በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው የደቡብ ጎንደር ዞን ለሚገኙ የፈርጣ፣ ጉና በጌምድር፣ ላይ ጋይንት እስቴና እብናት ወረዳዎች ለሚያስተምሩ መምህራን በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስተባባሪነትና በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አሰልጣኝነት በመሰጠት ላይ ነው፡፡
በስልጠናው የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ማተበ ታፈረ /ዶክተር/ ወራሪው የህውሃት ቡድን ለክልላችን እድገት ወሳኝ በሆነው የትምህርት ስርዓታችን ላይ ጉዳት ማደረሱን ገልጸዋል፡፡ መምህርነት በቅድመ ሁኔታ ያልተገደበ የሞራል ስራ በመሆኑን መምህራን ተማሪወችንና ህብረተሰቡን ከሃዘን፣ ቁዘማና ድባቴ በማውጣት ዉጤታማ የመማር ማስተማር ስራ ለማከናወን ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መምህራን ሁሌም ከችግሮች በላይ ርቀው በመብረር ትውልድ የመቅረጽ ሙያዊና ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት የመሪነት ሃላፊነት እንዳለባቸም ማተበ ታፈረ /ዶክተር/ ተናግረዋል፡፡
ክልላችን የበርካታ ጀግኖች መፍለቂያ መሆኑን ለትውልዱ በማስተማር በርካታ ጀግኖች በትምህርት ቤቶች እንዲፈጠሩ ማድረግ እንደሚገባም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
ለትምህርት ጥራት በርካታ ባለድርሻ አካላት ቢኖሩም የመምህራን ድርሻ ቀጥተኛ መሆኑን የገለጹት ቢሮ ሃላፊዉ መምህራን ትውልድንና ሃገርን በመገንባት ባለውለታና ባለእዳ በመሆናቸው በሃገርና ትውልድ ግንባታ ላይ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በወረራ የተያዙ የክልላችን አካባቢዎች ነጻ በሚወጡበት ጊዜ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን እየተከታተለ የደረሰውን የስነልቦና ጉዳት የሚጠግን ስልጠና እንደሚሰጥ ሃላፊው ቃል ገብተዋል፡፡
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት አነጋግረኝ ጋሻው /ዶክተር/ ወራሪው የህወሃት ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን በቆየባቸው ቀናት ለህሊና በሚከብድ መልኩ የተቋማትን፣ ግለሰቦችን ሃብትና ንብረት ማውደሙን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የመምህራን የስነ ልቦና ጥንካሬ ወደ ልጆችና ወላጆች የሚጋባ በመሆኑና ህብረተሰቡ በመምህራን ትልቅ እምነት ስላለው መምህራን በስነ ልቦና ጠንካራ በመሆን ህብረተሰቡን በማጽናናትና በማበረታታት የመሪነት ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የደብረ ታቦር ዩኒቨሪሲቲ በሚያስፈልገው ሁሉ ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን ፕሬዘዳንቱ ቃል ገብተዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ወንደሰን አቤ በበኩላቸው ጠላትን አሸንፈን የአማራ ክልል ህዝብ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲኖር የሁላችንም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ Amhara National Regional State Education Bureau
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse
ፌስቡክ https: Amhara Education Bureau