በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አዲስ በተዘጋጁ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሃፍት የተገቢነት ማረጋገጫ ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡
—————————————————————-
ባለፉት ዘመናት ሲተገበር የነበረው ስርዓተ ትምህርት በክህሎት፣ በስራ ፈጣሪነትና በስነ ምግባሩ ብቁ የሆነ ዜጋ ማፍራት አለመቻሉ በጥናት ከተለዬ በኋላ የመፍትሄ ሃሳቦች የተመላከቱበት አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በፍኖተ ካርታው ከተመላከቱ የመፍትሄ ሃሳቦች አንዱ የስርዓተ ትምህርት ለውጥ ማካሄድ ነው፡፡
በመሆኑም የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከአማራ ምሁራን መማክርት ጋር በተባበር በርካታ መምህራንና የትምህርት ምሁራን የተሳተፉበት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መማሪያና ማስተማሪያ መጽሃፍትን አዘጋጅቷል፡፡
በተዘጋጁት የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሃፍት ላይ በዘርፉ ምሁራንና አመራሮች የተገቢነት ማረጋገጫ ግምገማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
በግምገማ መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ማተብ ታፈረ /ዶክተር/ ሃገራችን አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ እንድትገኝ ያደረጋት ያለፈው ስርዓተ ትምህርት በመሆኑ ነጋችን የተሻለ ለማድረግ ጥራትና ተገቢነት ያለው ስርዓተ ትምህርት ለማዳባር ሃሳብ ያላቸውና ያገባኛል የሚሉ ሁሉ ሃሳባቸውን እንዲሰጡበት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ የአንደኛ ደረጃ ስርዓተ ትምህርት ለአንድ አመት በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በሙከራ የሚተገበር መሆኑን የገለጹት ሃላፊው በ2015 የትምህርት ዘመን በሙሉ ትግበራ ላይ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
በዩኒስኮ የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልክተኛ የሆኑት ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ስርዓተ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚያስተካክል ተቋማዊ ባለቤት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ከመምህራን ትምህርት ኮሌጆች ጋር በመቀናጀት አዲሱን የስርዓተ ትምህርት ሙከራና ትግበራ መከታተል እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡ የአማራ ክልል ህዝብ ከድህነትና ስራ አጥነት ለማላቀቅ የቅድመ መደበኛ ትምህርት፣ ሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ሙሁራን መማክርት የትምህርት ዘርፍና የመጽሃፍ ዝግጅት አስተባባሪ የሆኑት ዳዊት መኮንን /ዶክተር/ የአማራ ምሁራን መማክርት ጥራትና አግባብነት ያላቸውን መጽሃፍት ለማዘጋጀት መጣሩን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በአማራ ክልል የሚገኙ ምሁራንና መምህራን መጽሃፍ የማዘጋጀት አቅምና ልምድ መዳበር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ Amhara National Regional State Education Bureau
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse
ፌስቡክ https: Amhara Education Bureau