በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የሙከራ ተግበራ ላይ የመምህራን ሚና የጎላ ነው ተባለ::
==========================================
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የሙከራ ትግበራ ለማስጀመር የመምህራን ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምሁራንና የትምህርት ባለድርሻ አካላትን በስፋት ያሳተፈበት አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ በተመረጡ 30 ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ መምህራን በሶስት የስልጠና ጣቢያዎች የመፀሀፍት ትውውቅ ትናንት መሰጠት ተጀምሯል፡፡

በስልጠናው ማስጀመሪያ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ መኳንት አደመ በአዲሱ ስርአተ ትምህርት የሙከራ ትግበራ ላይ እንድትሳተፉ የተመረጣችሁ መምህራን የክልሉን መምህራንና ትምህርት ቤቶችን የምትወክሉ እና ለዚህ ስርዓተ ትምህርት የመጀመሪያዎቹ በመሆናችሁ ስልጠናውን በአግባቡ በመውሰድ የሙከራ ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የምትጫወቱት ሚና የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የተዘጋጁት መፀሀፍት በርካ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ቢሆንም የመማር ማስተማሩ ስራ ባለቤቶች እናንተ መምህራን በመሆናችሁ መፀሀፍቱን በአግባቡ በመተቸትና ጉድለቶችን ነቅሶ በማውጣት የተሻለ ግብአት መስጠት ይገባል ተብሏል፡፡
ባለፉት ስርዓተ ትምህርት የነበሩ ጉድለቶች እንዳይደገሙ ሁሉንም አካላት ያሳተፈ ስርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱ መልካም መሆኑን የተናገሩት መምህራን በዚህ የስርዓተ ትምህርት የሙከራ ትግበራ ተሳታፊ በመሆናችን ደስተኛ ነን ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት በመማር ማስተማሩ ሂደት ይገጥሙን የነበሩ ችግሮችን በሚፈታ ሁኔታ በትኩረት በመስራት የዜግነት ኃላፊነታችን እንወጣለን ያሉት መምህራን በቀጣይ ወደ ሙሉ ትግበራ በምንገባበት ጊዜ ያለፉት ጊዜአት ችግሮች እንደማይፈጠሩ ተናግረዋል፡፡
ከእንግሊዝኛና ስነዜጋ ትምህርቶች ውጭ ያሉ ሁሉም መምህራን ስልጠናውን እየወሰዱ ሲሆን በመጀመሪያ ደረጃ ሁለቱን የትምህርት አይነቶች ጨምሮ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስርዓተ ትምህርት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የሚዘጋጅ በመሆኑ በቀጣይ ጊዜአት የሙከራ ትግበራ እንደሚጀመር ይጠበቃል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ፌስቡክ https: Amhara Education Bureau
ዩቱዩብ Amhara National Regional State Education Bureau
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse