አዲስ በተዘጋጁ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት መመሪያ መጽሃፍት የመማር ማስተማር የሙከራ ትግበራ ተጀመረ::
አዲሱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት መማሪያና ማስተማሪያ መጽሃፍት በአማራ ምሁራን መማክርት አስተባባሪነትና በበርካታ ምሁራን ተሳትፎ መዘጋጀቱ ይታወሳል፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አዲስ በተዘጋጁት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የመማሪያ መጽሃፍት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው በአጼ ሰርፀ ድንግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር የሙከራ ትግበራ አስጀምሯል፡፡
የመማር ማስተማር የሙከራ ትገበራውን ያስጀመሩት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ማተብ ታፈረ /ዶክተር/ በሙከራ ትግበራው ወቅት መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች መጽሃፍቶቹን በትኩረት በማየትና በመገምገም ትውልድን የምንቀርጽበት የኛ የምንለው መጽሃፍ እንዲኖርን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በየመማሪያ መጽሃፍቱ ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ እያንዳንዱን ችግሮች ከተለዩና ማስተካከያ ከተደረገባቸው በኋላ በ2015 የትምህርት ዘመን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ሙሉ ትግበራ ላይ እንደሚውል ቢሮ ኃላፊው አመላክተዋል፡፡
በአጼ ሰርፀ ድንግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ተክለወልድ ብርሃን በሙከራ ትግበራው ወቅት የመመሪያ መጽሃፍቱ ሊኖሩባቸው የሚችሉ ክፍተቶች በመፈተሽና እንዲስተካከሉ አስተያዬት በመስጠት የተዋጣለት የመማሪያ መጽሃፍት እንዲሆኑ ለማስቻል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አዲስ በተዘጋጁት የመማሪያ መጽሃፍት በስድስት ዞኖች በተመረጡ 30 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሙከራ የመማር ማስተማር ትግበራ እንደሚካሄድ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ካሴ አባተ ገልጸዋል፡፡ በመጽሃፍቱ ዙሪያ የሙከራ ትምህርቱ በሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ መምህራን ስልጠና በመስጠትና ከ78 ሽህ በላይ የመማሪያ መጽሃፍት በባለሙሉ ቀለም ህትመት ታትመው መሰራጨታቸውን አቶ ካሴ ተናግረዋል፡፡
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያና ዌብ ሳይት አማራጮች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጠቀሙ ::
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *