የአማራ ህዝብ የተመረጡ እንቁ ልጆቹን የሚያስተምርበት የደሴ አዳሪ ትምህርት ቤት ከ23 ሚሊዬን ብር በላይ የሆነ የንብረት ዝርፊያና ውድመት ደርሶበታል
የአማራ ክልል ህዝብ ለበርካታ አመታት የተለዬ ተሰጣኦ ያላቸውን ልጆቹን የሚያስተምሩበት አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲከፈትለት ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ከመንግስት መልስ በማጣቱ ህዝቡ ቁጭት ውስጥ ቆይቷል፡፡ የአማራ ክልል ህዝቦች በራስ አቅም መልማትን ሰንቆ ህብረተሰቡን እያስተባበረ በሚሰራው የአማራ ልማት ማህበር /አልማ/ አስተባባሪነት ኢንጅነር ፀደቀ ይሁኔ በተባሉ ባለሃብት አማካኝነት ከ29 ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጭ የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተገንብቶ በ2011 ዓ.ም ትምህርት ጀምሮ ነበር፡፡
የነገ ሃገር መሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የቴክኖሎጅ አፍላቂ ምሁራንን ለማፍራት ታስቦ ትምህርት ቤቱ ሲከፈት በበርካቶች ዘንድ ትልቅ ተስፋ ፈንጥቋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት ይህ ትምህርት ቤት የሚተዳደርበት የራሱ ዝክረ ህግ አዘጋጅቶ ወደ ስራ እንዲገባ የራሱን ሚና ተወጥቷል፡፡ ለዚህ ትምህርት ቤት የወሎ ዩኒቨርሲቲ በየዘርፉ ስመ ጥር የሆኑና የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸውን መምህራን በልዩ ሁኔታ በመመደብ የኮምፒውተር፣ የፊዚክስ፣ የስነ ህይወትና የኬሚስትሪ ቤተ ሙከራዎችን እንዲደራጁ አድርጓል፡፡
የአማራ ልማት ማህበር /አልማ/ የተማሪዎችን ፍራሽ፣ አንሶላና ብርድ ልብስ አሟልቷል፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቤሮ ለአዳሪ ትምህርት ቤቱ የተሻለ ብቃትና ችሎታ ያላቸውን መምህራን በመመደብ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

በዚህ ትምህርት ቤት ከአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የተመረጡ 285 ባለልዩ ተሰጣኦ ተማሪዎች በመማር ላይ ነበሩ፡፡ ትምህርት ቤቱ በ2014 የትምህርት ዘመን ጥቅምት 25 ትምህርት ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቅቆ ተማሪዎቹን ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ ነበር፡፡
ነገር ግን አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን ደሴን ተቆጣጥሮ በቆየበት ወቅት ትምህርት ቤቱን እንዳልነበር አድርጎት ሸሽቷል፡፡
ስንት ወጭና ጉልበት የፈሰሰባቸውን የኮምፒውተርና የሳይንስ ቤተ ሙከራዎችን የቻለውን ዘርፎ ያልቻለውን አውድሟል፡፡ የተማሪዎች ማደሪያ ዶርም ውስጥ የነበሩ አልጋ፣ ብርድ ልብስ፣ ፍራሽ ዝርፏል፡፡
የተማሪዎች መታከሚያ ክሊኒክ ውስጥ የነበሩ መድሃኒትና የላባላቶሪ እቃዎችን ወስዷል፡፡
ለተማሪዎች ቀለብ የተዘጋጀ ጤፍ፣ ሽሮና በርበሬ ዘርፏል፡፡ የተማሪዎችን መመገቢያ ማንኪያ እንኳን ሳያስቀር ወስዷል፡፡
በትምህርት ቤቱ በአጠቃላይ ከሃያ ሶስት ሚሊዬን ብር በላይ የሚያወጡ ንብረቶች በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን ዝርፊያን ወድመት መደረሱን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ በለጠ ሃይሌ ነግረውናል፡፡
የትምህርት ቤቱን መውደምና መዘረፍ የሰሙ ተማሪዎችና መምህራን ማዘናቸውን የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር አለምነው አበራ ገልጸዋል፡፡ አሸባሪው የህውሃት ቡድን በቅናትና በምቀኝነት ትምህርት ቤቱን እንዳልነበር አድርጎታል፡፡ በተማሪዎችና መምህራን ዘንድ ቁጭትን ፈጥሯል፡፡
ይሁንና የነገ ተስፋ የሰነቅንባቸው እንቁ ተማሪዎቻችን የሚማሩበት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ወደ ቀድሞ የመማር ማስተማር ስራው እንዲመለስ የሁላችንም ድጋፍ ይሻል፡፡
በትግራይ አሸባሪና ወራሪ ሃይል የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት እኔም ድርሻ አለኝ!!
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያና ዌብ ሳይት አማራጮች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጠቀሙ ::
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse