ጁንታው አተርፍናቸው ያልናቸውን ልጆቻችንን አሳጥቶናል፡፡
ለበርካታ አመታት ትምህርት የተጠማችው ከተማ፡፡ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገነባላት ኮሚቴ አዋቅራ ለመንግስት ጥያቄዋን ስታቀርብ ቆይታለች፡፡ ነገር ግን ሰሚ ጆሮ አላገኘችም፡፡
ተስፋ የቆረጡት ልጆቿ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን እንዳጠናቀቁ በበረሃና በውቅያኖስ መሰደድን መረጡ፡፡ በዚህም በርካቶች ለአውሬና ለአሳ ነባሪ ሲሳይ ሆነዋል፡፡ የነገን ተስፋ የሰነቁ ሌሎች ህጻናት ደግሞ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመማር በሚጣጣሩበት ወቅት ሴት ተማሪዎች መደፈራቸው የልጃገረዶችን የነገ ተስፋ አዳጋች አደረገባቸው፡፡
የከተማዋ ማህበረሰቦች በጋራ መከሩና በድጋሚ ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች በመምረጥ ለመንግስት ጥያቄ የሚያቀርቡ ሶስት አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቀሩ፡፡
እነዚህ የከተማው ሶስት ጉምቱ ሽማግሌዎች ከህዝብ የተቀበሉትን አደራ ተሸክመው መንግስት ጥያቄያችንን ተቀብሎ ትምህርት ቤት ይገንባልናል የሚለውን ተስፋ አንግበው ጉዞአቸውን ወደ ባህር ዳር አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ቀንን አያውቁ ነውና ነገሩ በጉዟቸው ላይ እንዳሉ የጨለቃ በተባለች ቦታ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ የከተማዋን አደራ እንደያዙ ሶስቱም ሽማግሌዎች ህይወታቸው አለፈ፡፡
ይህች የእውቀት ጥማቷን ጥያቄ እንዲመለስላት ለጉምቱ ሽማግሌዎቿ አደራ ሰጥታ የላከች ነገር ግን ምላሿን እንኳን ሳትቀበል አስታራቂና መካሪ አባቶቿን ያጣች በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የምትገኘው የገርባ ከተማ ለእውቀት ጥማት የተከፈለ መስዋእትነት ታሪክ ነው፡፡
የገርባ ነዋሪዎች ጎምቱ አባቶቿ በከፈሉት መስዋእትነት ለቁጭት ተዳረጉ፡፡ እናም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በራሳቸው አቅም ለመስራት ተስማሙ፡፡ ህዝቡ ከእለት ጉርሱ እያዋጣ የጉልበት ስራውን በወረፋ እየሰራ ከ ዘጠኝ ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጭ 12 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለ ሁለት ወለል ህንጻ ገንብቶ ትምህርት ቤቱን ስራ አስጀመረ፡፡ እኒህ ትጉ ወላጆች ከትምህርት ቤት ግንባታው በተጨማሪ በሌላ አለም ላይ የሚኖሩ የአካባቢውን ተወላጆች ሁሉ አስተባብረው ለተማሪዎች መማሪያ የሚሆን መጽሃፍትን፣ የቤተ ሙከራ እቃዎችን፣ ኮምፒውተሮችን ለትምህርት ቤቱ አሟሉ፡፡
ነገር ግን የአማራ ክልልና የአፋር ክልልን የወረራው አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን ይህን የገርባ አልነጃሽ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጦር ካምፕና የቁስለኞች የህክምና ማእከል አደረገው፡፡
አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ሃይል የገርባ ነዋሪዎች በላባቸው ሲሚንቶ አቡክተው በደማቸው አሸዋ ከስክሰው ከልጆቻቸው የእለት ጉሮሮ ቀንሰው የገነቡትን ትምህርት ቤት በውስጡ የነበሩትን ኮምፒውተሮች ዘረፈባቸው፣ መጽሃፍትን በሙሉ አቃጠለባቸው፣ ወንበሮችን ፈልጦ የምግብ ማብሰያ አደረጋቸው፣ የቤተ ሙከራ ክፍሎችን አወደማቸው፡፡
ይባስ ብሎ ትምህርት ቤቱ ውስጥ የተማሪዎች የመማሪያ ክፍል አጠገብ በርካታ የሞቱ ወታደሮቹን አስክሪን ቀብሮበታል፡፡ አሸባሪው ቡድን የትምህርት ቤቱን ግቢ ከእውቀት ገበያነት ወደ መካነ መቃብርነት ቀይሮታል፡፡ ከ60 በላይ የጅምላና የተናጥል መቃብሮች በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ቀብሮ ሸሽቷል፡፡ አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በአግባቡ እንኳን አፈር ያላለበሳቸው አስክሬኖችን ጅብ እያወጣ በማስቸገሩ ምክንያት የገርባ ወላጆች ዛሬም የጅምላ መቃብሮችን ጥበቃ ላይ ናቸው፡፡





የገርባ ከተማ የሃይማኖት መሪና የትምህርት ቤቱ አሰሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ሼህ አህመድ ሁሴን አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከስደት፣ ከመደፈርና ከመሃይምነት አተርፍናቸው ያላቸው ልጆቻችንን አሳጥቶናል ይላሉ፡፡ አስክሬን የተቀበረበት ቦታ እንኳን ህጻናት ትልቅም ሰውም ይፈራል የህጻናት አእምሮ ደግሞ እንደነጭ ወረቀት በመሆኑ ወደ ትምህርት ቤት መጥተው ለመማር የስነ ልቦና ጫና ደርሶባቸዋል ይላሉ፡፡ ወላጅም አምኖ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤቱ ለመላክ እንደሚቸገሩ ይናገራሉ፡፡
ይህ አሸባሪ ቡድን እንኳን ለኢትዮጵያና ለአማራ ህዝብ ይቅርና ለትግራይ ልጆችም አያዝንም የሚሉት ነዋሪዎቹ የአካባቢያቸውን መውጫና መግቢያ እንኳን በቅጡ የማያውቁ የትግራይ ህጻናትን አምጥቶ ትምህርት ቤታችን ውስጥ ቀብሯቸው በመሄዱ ማዘናቸውን ይናገራሉ፡፡
ነዋሪዎቹ እንደ አካባቢያቸው ባህልና ሃይማኖት መሰረት የሰው ልጅ ሲኖር መኖሪያ ቤት እንዳለሁ ሁሉ ሲሞትም የተከበረ የቀብር ቦታ ያለው በመሆኑ መንግስት በትምህርት ቤታቸው ያሉ ቀብሮችን አንስቶ ወደ ቀብር ቦታ ተውስደው እንዲቀበሩ ትብብር እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
በትግራይ አሸባሪና ወራሪ ሃይል የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት እኔም ድርሻ አለኝ!!
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያና የዌብ ሳይት አማራጮች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጠቀሙ ::
ፌስቡክ Amhara-Education-Bureau
ዩቱዩብ UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse