በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ ምክንያት በወደሙ ትምህርት ተቋማትና የትምህርት አጀማመር ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡
ውይይቱ በወረራ ውስጥ የቆዩ የዞንና ወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት በደሴ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ወቅት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ማተብ ታፈረ /ዶክተር/ ወራሪው የህውሓት ሃይል አማራን ለመበቀል በማሰብ በትምህርት ተቋሞቻችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማደረሱን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የትምህርት አመራሩ፣ መምህራንና መላው ህብረተሰብ የተዘረፉና የወደሙትን መልሶ በመገንባት ወደ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራ መመለስ እንደሚቻል ተናገረዋል፡፡
ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች ርብርብ እንዲያደርጉ ማተብ ታፈረ /ዶክተር/ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዚህ ወቅት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁጭት ስሜት፣ ፈተናን በጥበብ በማለፍ፣ ከችግር በፍጥነት በመውጣት ታሪክ መስራትና የህብረተሰቡን ከፍታ ማስጠበቅ እንደሚገባ ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ የትምህርት ተቋማት የደረሰባቸውን ዝርፊያና ውድመት ለወላጆችና ለየአካባቢያቸው ህብረተሰብ በግልጽ በማሳወቅ ድጋፍ እንዲያደርጉ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ ቢሮው በበኩሉ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ጉዳት ለደረሰባቸው የትምህርት ተቋማት የተቻለውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት አመራሮች በበኩላችው በትምህርት ተቋማት ላይ በደረሰው ጉዳት ከማዘን ወጥተው ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት በማምጣት ከመምህራን ጋር የጋራ መግባባት በመፍጠር ያለፉ የትምህርት ጊዚያትን ለማካካስ እንደሚሰሩ ተናገረዋል፡፡