በሙከራ ትግበራ ላይ የሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሃፍት ግምገማ ተካሄደ፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከአማራ ምሁራን መማክርት ጋር በመተባበር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሃፍት ተዘጋጅቶ በ62 ትምህርት ቤቶች በሙከራ ትግበራ ላይ ይገኛል፡፡
የሙከራ ትግበራ ከሚካሄድባቸው ትምህርት ቤት መምህራን፣ ር /መምህራን፣ ሱፐር ቫይዘሮች፣ ከወረዳ፣ ከዞን ትምህርት አመራሮችና ከመጽሐፍት አዘጋጆች ጋር በደብረ ታቦር፣ በእንጅባራና በደብረ ማርቆስ ከተማ ግምገማ ተካሂዷል፡፡
በሙከራ ትግበራው ሂደት መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ወላጆችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መጽሐፍቱን የበለጠ ለማበልጸግና ለማሻሻል ሃሳቦች መስጠታቸውን በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሂሳብና ሳይንስ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ጋሻው ክንዴ ገልጸዋል፡፡ ቢሮው አተገባበሩን በሚመለከት በምልከታ የታዘበውንና ከመምህራን፣ ተማሪዎችና ከህበረተሰቡ ያገኘውን የማሻሻያ ሃሳቦች ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የጋራ መደረጉን አቶ ጋሻው አመላክተዋል፡፡
በግምገማው መጽሃፍቱን ለማበልጸግና ለማሻሻል የሚያግዙ አስተያዬቶች መገኘታቸውን የአማራ ምሁራን መማክርት ሰብሳቢ ዶክተር ዳዊት መኮንን ገልጸዋል፡፡ የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሐፍ ማዘጋጀት በክልሉ የመጀመሪያ በመሆኑ በዝግጅቱና በሙከራ ትግበራው ወቅት በርካታ ልምዶች መገኘታቸውንም ዶክተር ዳዊት አስረድተዋል፡፡
በምልከታና በግምገማ የተገኙ ሃሳቦችን በመጽሐፍት ክለሳው ወቅት በማካተት ጥራት ያላቸውና በትክክል ትውልድን መገንባት የሚያስችሉ የመማሪያና የማስተማሪያ መጽሐፍት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬከተር አቶ ካሴ አባተ ተናግረዋል፡፡
በሙከራ ትግበራ ላይ የሚገኙት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሐፍት ላይ ክለሳና ማሻሻያ በማድረግ በ2015 የትምህርት ዘመን ወደ ሙሉ ትግበራ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
በመጽሃፍቱ ላይ አስተያየት መስጠት ለምትፈልጉ ሁሉ በዌብ ሳይት አድራሻችን https://www.anrseb.gov.et/downloads/new-textbooks/ በዚህ ሊንክ በመግባት የመማሪያ መጽሃፍቱን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያና ዌብ ሳይት አማራጮች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጠቀሙ ::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *