የእነሴ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ7 ነጥብ በ 9 ሚሊዩን ብር ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ፤ የትምህርት ቤቱ መገንባት ችግራቸዉን እንደሚቀርፍላቸዉ ተማሪዎችና ወላጆች ተናግረዋል፡፡
*****************
በምስራቅ ጐጃም ዞን በሁለት እጁ እነሴ ወረዳ የእነሴ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአማራ ልማት ማህበር አልማ በ7 ነጥብ 9 ሚሊዬን ብር የማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቅቆ ለምረቃ በቅቷል፡፡ትምህርት ቤቱ 1ዐ ክፍሎች ያሉት ባለ አንድ ፎቅ እና ዘመናዊ ቤተሙከራን ያካተተ ሲሆን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 22 ወራትን ፈጅቷል፡፡ ከዚህ በፊት የተገነቡ ሌሎች ክፍሎቹን ጨምሮ ትምህርት ቤቱ 4 ሽህ 4ዐዐ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ ሆኗል፡፡
ከዚህ በፊት በአንድ ክፍል ውስጥ 9ዐ ተማሪ ሆነን ስንማር በትምህርት አቀባበላችን ላይ ችግር ፈጥሮብን ነበር ያለው የእነሴ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ አማንኤል ዋለ በአሁኑ ሰዓት ዘመናዊ ቤተሙከራና የመማሪያ ክፍል በመገንባቱ ችግራችንን ይቀርዋልና ካለ በኃላ የተደራጀ የአይሲቲ ክፍልም እንደሚያስፈልግ ተናግሯል፡፡
የዚሁ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት መምህርት ስመኝ አየነው በበኩላቸዉ በክፍል ጥበት ምክንያት በአንድ ክፍል ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ በመኖሩ ለቁጥጥርና ለትምህርት ጥራት እንቅፋት ከመሆኑም በላይ የማካካሻ ትምህርት ለመስጠት እንቸገር ነበር፤ ቤተ ሙከራው እና ክፍሎቹ መገንባታቸዉ ለትምህርት ጥራቱ ከፍተኛ አስተዋፆ አላቸዉ ብለዋል፡፡
በሁለት እጁ እነሴ ወረዳ የጓትራ ቀበሌ ኗሪ አቶ ጀግናው አድማስ አማራ ልማት ማህበር (አልማ) ከ2ዐዐ4 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የትምህርት ተቋማትን ገንብቶልናል፤ እኔም የአልማ አባል ነኝ፡፡ ያወጣሁትን ገንዘብ ተግባር ላይ ሲውል በማየቴ ደስ ብሎኛል፤ ልጀም በዚህ ትምህርት ቤት ትማራለች ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መዝገብ አንዱአለም በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት አልማ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም አካባቢዎች ትምህርትቤቶችን እየገነባ ነው፤ ይህን የእነሴ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2ዐዐ4 ዓ.ም በ2 ነጥብ 8 ሚሊዩን ብር ከባለሀብቶች ገዝተን አሁን ደግሞ የማስፋፊያ ግንባታውን ጨምረን የትምህርት ጥራት እንዲመጣ እየሰራን ነው፡፡ ሀገርን በሚገነባ የተማረ የሰው ሀይል በመሆኑ አልማ በሰው ሀብት ልማት ላይ በተለይ ትምህርት ቤት ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራን ነው ያሉት አቶ መዝገቡ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ተቋማት መልሶ በመገንባትና ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን በዕለት ምግብ አቅርቦት ላይ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
የምስራቅ ጐጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስለሽ ተመስጌን በበኩላቸዉ አልማ በዞኑ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ 88 ብሎክ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ አስረክቧል፤ በግንባታ ላይም ያሉ አሉ፤ በተማሪ ቁጥር ብዛትና በክፍል ጥበት ምክንያት የተማሪ ክፍል ጥራትና እና በተግባር ትምህርት አሰጣጥ ላይ ችግር ተፈጥሮ ነበር፤ ከ2ዐ12 ዓ.ም ጀምሮ አልማ ችግሮችን እየፈታልን ነው፤ ተጠናክሮም መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
ምንጭ ምስራቅ ጎጃም ዞን ኮሙዩኒኬሽን
የወደሙ ትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አቅምዎ የፈቀደውን የብር መጠን ጽፈው ወደ 9222 ይላኩ።
በቴሌብር ድጋፍ ለማድረግ የቴሌብር ቁጥራችን 9222 ን ይጠቀሙ በተጨማሪም በቴሌብር ዓለምአቀፍ ሀዋላ ከውጭ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ 0993161616 በመጠቀም የድርሻዎን ይወጡ።
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያና ዌብ ሳይት አማራጮች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጠቀሙ ::
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse