ግሎባል አሊያንስ ከልማት ማኅበራት ጋር በመሆን በሰቆጣ ከተማ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሊገነባ ነው።
ግሎባል አሊያንስ ከአማራና ዋግ ልማት ማኅበራት ጋር በመሆን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ ለሚገነባው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።
በትምህርት ቤቱ ግንባታ በፍሎሪዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተሳታፊ መሆናቸው ተመልክቷል።
የአማራ ልማት ማኅበር ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፋንታ እንዳሉት አሸባሪው ትህነግ በክልሉ በፈፀመው ወረራ ምክንያት ከሰብዓዊ ጉዳት ባሻገር ቁሳዊ ውድመት ደርሷል።
የሽብር ቡድኑ በርካታ ተማሪዎች እውቀት የሚገበዩባቸውን የትምህርት ተቋማት ጭምር ማውደሙን ገልጸዋል።
ተማሪዎች ከጦርነት እሳቤ ወጥተው ቀጣይ ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ መገንባት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በትብብር የሚገነባው ትምህርት ቤት በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በየደረጃው ያሉ የመንግስት አመራሮች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በግሎባል አሊያንስ የቦርድ አባልና የፍሎሪዳ አስተባባሪ አቶ ከፍያለው ፍቃደ በበኩላቸው የግሎባል አሊያንስ ለተጎዱ ወገኖች ከሚያደርገው የሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር የወደሙ ተቋማትን መልሶ ግንባታ ላይ ይሰራል።
በፍሎሪዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በጦርነቱ የወደመ ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን ተናግረዋል።
“የወደሙ ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ፤ ልጆችም ይማራሉ” በሚል መርህ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን እያስተባበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዋግ ልማት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ አምላኩ አበበ በበኩላቸው በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“በትብብር የሚገነባው ትምህርት ቤት ህፃናትን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የሚያግዝ ነው” ብለዋል።
የትምህርት ቤቱ ግንባታ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደሚደረግበት የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በግንባታው የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ ሙከራ፣ የመምህራን ቢሮና መፀዳጃ ቤቶች መካተታቸውን ተናግረዋል።
”የወደሙ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማት መልሶ መገንባት ለነገ የማይባል ተግባር ነው” ያሉት ደግሞ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን ናቸው።
ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ በመቀመጡ አመስግነዋል።
ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንዲወጡ አቶ ሹመት ጠይቀዋል።
(አሚኮ)
የወደሙ ትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አቅምዎ የፈቀደውን የብር መጠን ጽፈው ወደ 9222 ይላኩ።
በቴሌብር ድጋፍ ለማድረግ የቴሌብር ቁጥራችን 9222 ን ይጠቀሙ በተጨማሪም በቴሌብር ዓለምአቀፍ ሀዋላ ከውጭ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ 0993161616 በመጠቀም የድርሻዎን ይወጡ።
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያና ዌብ ሳይት አማራጮች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጠቀሙ ::
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse