የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው
በደቡብ ወሎ ዞን ለሚገኙ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሥራ የሚረዱ ከ2 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የትምህርት መገልገያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ በደቡብ ወሎ ዞን የትግራይ አሸባሪ ቡድን ጉዳት ያደረሰባቸው የትምህርት ተቋማትን የመማር ማስተማር ሂደት ለማስጀመር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ከ2 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የቢሮ መገልገያና ለተማሪዎች መማሪያ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉ ኮምፒውተር፣ ጥቁር ሰሌዳ፣ የተማሪዎች ደብተር ፣ እስኪቢርቶ፣ አጋዥ መጽሐፍት፣ ወንበርና ጠረንጴዛ እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ መገልገያ ቁሳቁሶች ናቸው።
ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ም/ ኃላፊ አቶ ዓለምነው አበራ በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በመምህራንና በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ጫናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማድረሱን ጠቁመዋል።
ከወረራው በኋላ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆን ስለሌለባቸው ት/ቤቶችን በማጽዳትና በተወሰኑ ግብዓቶች ትምህርት የማስጀመር ስራ መሰራቱን አስረድተዋል።
የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ወደ መማር ማስተማር ሂደት ለማስገባት የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እያደረገ እንደሆነ አቶ ዓለምነው አብራርተዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ያደረገው ድጋፍም በአሸባሪው ጉዳት የደረሰባቸው የትምህርት ተቋማትን ወደ መማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ለማስገባት እየተደረገ ላለው ጥረት አቅም ይሆናል ብለዋል።
ለተደረገው ለተማሪዎች መማሪያና የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ አመስግነው ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር አካላትም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ነው ጥሪ ያቀረቡት።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ም/ ኃላፊ ወ/ሮ ደጀጥኑ ከበደ በበኩላቸው የምዕራብ ጎጃም ህዝብ በህልውና ዘመቻው ላይ በግንባር ከመፋለም ጀምሮ የተለያዩ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከ2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ተቋሙን ወደ ሥራ ማስገባት የሚችሉ የተለያዩ የተማሪዎች መማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው በቀጣይም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።
በዞኑ የሚገኙ 504 ት/ ቤቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃና በከፊል ያላቸው ቁሳቁስ ከፍተኛ ውድመት የደረበት ሲሆን ከ583 ሚሊየን ብር በላይ ኪሳራ ማድረሱን ከደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ደቡብ ወሎ ኮሙኒኬሽን
የወደሙ ትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አቅምዎ የፈቀደውን የብር መጠን ጽፈው ወደ 9222 ይላኩ።
በቴሌብር ድጋፍ ለማድረግ የቴሌብር ቁጥራችን 9222 ን ይጠቀሙ በተጨማሪም በቴሌብር ዓለምአቀፍ ሀዋላ ከውጭ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ 0993161616 በመጠቀም የድርሻዎን ይወጡ።
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያና ዌብ ሳይት አማራጮች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጠቀሙ ::
በቴሌግራም https://t.me/anrse