በአማራ ክልል ለ2ኛ ጊዜ የትምህርት ብርሃን ምዘና ሊሰጥ ነው
=========================================
በአማራ ክልል ማንበብ፣መፃፍና ማስላት ለሚችሉ ጎልማሶች ለ2ኛ ጊዜ የትምህርት ብርሃን ምዘና ሊሰጥ ነው፡፡
የትምህርት ብርሃን ምዘናው የሚሰጠው በመደበኛው የትምህርት መርሃ ግብር መማር ያልቻሉና በጎልማሶች ትምህርት፣በራሳቸው ጥረት ወይም በሌሎቹ እገዛና በሀይማኖታዊ ትምህርቶች ማንበብ፣መፃፍና ማስላት ለሚችሉ ጎልማሶች በፈቃደኘነት ላይ መሰረት ያደረገ ምዘና እንደሚሰጥ ነው የተገለፀው፡፡
የምዘና ሂደቱን አስመልክቶ ከሰሞኑ በደብረ ታቦር ከተማ ከሁሉም ዞን ትምህርት መምሪያዎች የጎልማሶች ትምህርት ቡድን መሪዎችና ምዘናው ከሚሰጥባቸው ወረዳዎች የተውጣጡ የጎልማሶች ትምህርት ባለሙያዎች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡
ምዘናውን በውጤታማነት ለማጠናቀቅ በሚያስችልበት ሁኔታ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የምዘና ጊዜውም ከሚያዝያ 10 እስከ 12/2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ወረዳዎቹ ውይይት በማድረግና የሚመቸውን ቀን በመምረጥ ምዘናው እንደሚሰጥ በውይይቱ የተገኙት በትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሴ አባተ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በዚህ ዙር 5 ዞኖች ምዘናው የማይሰጥባቸው ሲሆን ምዘናው በሚሰጥባቸው ዞኖች ከ85ሺህ በላይ ጎልማሶች ምዘናውን እንደሚወስዱ ይጠበቃል፡፡
በሰ/ወሎ፣ዋግህምራ፣በደ/ወሎ፣በደሴ ከተማና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች በዚህ ዙር ምዘናው የማይሰጥ ሲሆን በቀጣይ ሰኔ ወር ምዘናው እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡
በውይይት መድረኩ የክልሉ የጎልማሶች ትምህርት እንቅስቃሴም ተገምግሞ የቀጣይ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *