የ2013 የትምህርት ዘመን 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት አስመልክቶ ባቀርብናቸው ቅሬታዎች ላይ የተደረሰበት ሂደት አጭር መረጃ !!
1. በጦርነት አውድ ውስጥ ቆይተው ፈተና እንዲወስዱ የተደረጉ ተማሪዎች በውጤታቸው ላይ የተለየ ተፅዕኖ የተፈጠረ መሆኑ እና ጉዳዩ በልዩ ሁኔታ መታየት እንዳለበት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር አስፈላጊው መግባባት ተፈጥሯል፡፡
2. በትምህርት ቢሮው በኩል በጦርነት ተጽዕኖ ምክንያት ውጤታቸው የቀነሰባቸው ተማሪዎች ዝርዝር መረጃ እና አስፈላጊ ማስረጃዎች ሁሉ ለትምህርት ሚኒስቴር ቀርበዋል፡፡
3. ትምህርት ሚኒስቴርም በቀረበለት መረጃ እና ማስረጃ መሰረት ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ እያየው እንደሆነ እና ውሳኔውን በቅርብ ቀናት የሚያሳውቅ መሆኑን ገልዿል፡፡
ማሳሰቢያ፡- ከላይ ከተጠቀሱት ሶስት ጭብጦች በተጨማሪ መረጃ ለሚፈልግ አካል በፈተና ሂደቱ ላይ የቀረቡ ቅሬታዎችን እንዲያጣራ የተላከው ኮሚቴ ዝርዝር መረጃ ከዚህ በታች የቀረበ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
ኮሚቴው መረጃዎችን በአግባቡ አደራጅቶ ወደ ፈተናዎች ኤጀንሲ በመሄድ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ምርመራ አድርጓል፡፡
 ከፈተና እርማት ጋር በተያያዘ ሊኖር ይችላል ብሎ የገመተውን ችግር ለመመርመር ጥረት አድርጓል፡፡ ኮሚቴው ባደረገው ማጣራት በአንዳንድ ተማሪዎች ላይ የተከሰተው የውጤት ልዩነት የፈተና እርማት ችግር ሳይሆን ፈተናው በሁለት ዙር ከመሰጠቱ ጋር ተያይዞ የተማሪዎች ውጤት ሲተላለፍ የተከሰተ ቴክኒካል ችግር እንደሆነ እና ችግሩ በሌሎች ክልሎች ተማሪዎችም በተወሰነ ደረጃ ተከስቶ እንደነበርና ማስተካከያ እንደተደረገበት አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም የሁሉም ተማሪዎች ውጤት ሰርቨር ላይ በትክክል የተመዘገበ ስለሆነ ካርዳቸው ታትሞ ሲወጣ ትክክለኛ ውጤታቸው እንደሚሆን አረጋግጧል፡፡
 ቢሮው ቀድሞ ለተማሪዎች ውጤት መቀነስ ምክንያት ይሆናሉ ብሎ ከለያቸው መላምንቶች መካከል የፈተና እርማት ችግር፣ የፈተና ስርቆት፣ ተማሪዎች በጦርነት አውድ ውስጥ ሆነው መፈተናቸው ይገኝበታል፡፡
 ኮሚቴውም ከእነዚህ መላምንቶች ተነስቶ አስፈላጊ መረጃዎችን በመሰብሰብና በመተንተን የደረሰበት ድምዳሜ ተማሪዎች በጦርነት አውድ ውስጥ ቆይተው መፈተናቸው ለውጤታቸው መቀነስ እንደ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
 የኮሚቴው ሪፖርትም ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሚመለከተው የክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲደርስ ተደርጓል፡፡
 ትምህርት ሚኒስቴር ከቀረበው ሪፖርት እና ከቢሮው ከቀረበለት ቅሬታ በመነሳት ከየክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረገው ውይይት ሌሎች መለስተኛ ችግሮች በፈተና ሂደቱ ላይ የነበሩ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለተማሪዎች ውጤት መቀነስ ዋናው ምክንያት ተማሪዎች በጦርነት አውድ ውስጥ ቆይተው መፈተናቸ መሆኑን ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
 በመሆኑም ትምህርት ሚኒስቴር ችግሩን ተረድቶ በቅርብ ቀን መፍትሄ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
ስለሆነም
 ተማሪዎች፣ወላጆችና መላው ማህበረሰብ የትምህርት ሚኒስቴርን የመፍትሄ ሃሳብ በትግስት እንዲጠብቁ ቢሮው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
 የ2014 ትምህርት ዘመን የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች በተፈጠረው ችግር ሳይዘናጉ በልህና ቁጭት በመዘጋጀት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንዲዘጋጁ ቢሮው ጥሪውን ያቀርባል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *