በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ያካባቢው ተወላጆችና አጋር አካላት የቆቦ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ
የቆቦ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በክልሉ ከፍተኛ ተማሪ ቁጥር ከሚያስተናግዱ ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ ቀደምት ትምህርት ቤትና በርካታ ምሁራንን ያፈራ ሲሆን በተሻለ ደረጃ ከተደራጁ ትምህርት ቤቶች መካከል የሚጠቀስ ነበር፡፡
የተደራጀ የቤተሙከራ፣የአይሲቲ ክፍል፣የክላውድ ኮመፒቲነግ፣ የኢለርኒግና የፕላዝማ ትምህርት በተደራጀ ሁኔታ ይሰጥ እንደነበር የትምህርት ቤት መምህራንና ተማሪዎች ይናገራሉ፡፡ በአሁ ሰዓት ሁሉንም ግብአቶች በመዝረፍና በማውደም አሸባሪው ቡድን ቆቦ ምሁር እንዳታፈራ የክፋት ጥጉን አሳይቷል፡፡
ከ4ሺህ በላይ ተማሪዎችን የሚያስተናግደው የቆቦ አጠ/2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጉዳት ከደረሰበት በኋላ የትምህርት ቤቱ እና የከተማው ማህበረሰብ በመተባበር ትምህርት በማስጀመር የመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡
የቆቦ አጠ/2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ር/መምህር አቶ መሰለ በላይ ትምህርት ቤቱ በእጅጉ የተጎዳ በመሆኑ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖር የአካባቢው ተወላጆችና አጋር አካላት የቆቦ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ነበረበት እንዲመለስ በሚደረገው ርብርብ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሸባሪ ቡድን በቆቦ ከተማ በየሚገኙ የመጀመሪያና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጉዳቱ የከፋ በመሆኑና የተገኙ ድጋፎች ጊዜአዊ ትምህርት ለማስጀመር በመሆኑ የከተማውን ትምህርት ቤቶች ወደ ነበሩበት አቋም ለመመለስ የአካባቢው ተወላጆች፣ባለሀብቶች፣አጋር አካላትና የቀድሞ ተማሪዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ የከተማ አስተዳደሩ ም/ከንቲባና ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ሀይላቭ ወንድሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መምህራንና ማህበረሰቡ በቁጭት በመነሳሳት በገንዘብ፣በጉልበትና በቁሳቁስ ትምህርት ቤቶችን ድጋፍ በማድረግ ላሳየው ተነሳሽነት ምስጋና ያቀረቡት ኃላፊው የክልሉ ትምህርት ቢሮና አልማ ትምህርት ለማስጀመር እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ጠላት የስነልቦና ጫና ለመፍጠር በትምህርት ቤቶች የተለያዩ ጹፎችን በመፃፍ ተማሪዎችና መምህራን በስነልቦና እንዲጎዱ ቢሰራም ጹሁፎችን በማጥፋት እና ትምህርት ቢሮውና አጋር ድርጅቶች የስነልቦና ስልጠና በመስጠት መምህራንና ተማሪዎች ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ እገዛ እንዳደረገ አክለው ገልጸዋል፡፡