የቅድመ መደበኛ ትምህርትን በጨዋታ ማስተማር የህፃናትን የአካል፣ የስነ ምግባር፣ የአእምሮ፣ የማህበራዊ፣ ስሜታዊና ሁለንተናዊ እድገት ለማጎልበት የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገለጸ፡፡

ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተዉ የሰሩ ሀገራት በዘርፉ ትኩረት ካልሰጡት የተሻለ ዉጤታማ መሆናቸዉን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በሃገራችን ብሎም በክልላችን ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ትኩረት ቢሰጥም እድገቱ ግን በሚፈለገው ደረጃ ገና አልደረሰም፡፡ ለዚህም በርካታ ችግሮች የሚጠቀሱ ቢሆኑም የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች የሚማሩበት የመማር ማስተማር ሂደትና የማህበረሰቡ ግንዛቤ አለማደግ ዋነኛ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ህጻናት በአንድ ነገር ላይ ሊኖራቸው የሚችለው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑ ህጻናትን ለማስተማር ጨዋታ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

በአማራ ክልል ሁለት ወረዳዎች ሌጎ ፋውንዴሽን /LEGO Foundation / የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የቅደመ መደበኛ ተማሪዎች በጨዋታ መማር የሚችሉበትን የመማር ማስተማር ሂደት ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኝት ቁጥር አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የቅድመ መደበኛ መምህር የሆኑት ገዳሜ ሞገስ ቀደም ሲል በዚህ ትምህርት ቤት ህፃናትን ያስተምሩ እንደነበር በማስታዎስ ህፃናት ቁጥሮችን እንዲለዩ፣ እንዲፅፉና እንዲያነቡ ለማድረግ ከአቅማቸዉ በላይ የሆኑ ነገሮችን ያስሯቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይህ የማስተማር ስልት ግን ልጆቹ ትምህርቱንና ትምህርት ቤቱን እንዲጠሉት አድርጓቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡

ነገር ግን ለህጻናቱ ጨዋታን መሰረት ያደረገ ትምህርት መስጠት ከጀመሩ ወዲህ በህጻናቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማየታቸውን መምህሯ ነግረውናል፡፡ ህፃናትን በመዝሙር፣ በተለያዩ የክፍል ዉስጥና የክፍል ዉጭ ጨዋታዎች በማጫወት፣  የትምህርት መሳሪያዎችን እንዲነካኩና እንዲገጣጥሙና እንዲለያዩ በማድረግ፣ አካባቢያቸዉን እንዲቃኙ፣ በአደጋ ጊዜ እራሳቸዉን እንዲከላከሉ በጨዋታ ስለሚማሩ የትምህርት ፍቅር እንዲኖራቸዉ፣ አካላቸዉና አእምሯቸዉ እንዲዳብር፣ ማህበራዊ ግንኙነታቸዉ ስኬታማ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

እንደ መምህርቷ ገለጻ ልጆች በተለያዩ የጨዋታ ዘዴዎች ሲማሩ ጨዋታቸውን ከትምህርት ይዘቱ ጋር በቀላሉ ለማገናዘብ እንድሚያግዛቸው አመላክተዋል፡፡ ወላጆችም በየጊዜው በልጆቻቸው ላይ በሚያስታውሉት ለውጥ ዙሪያ ከመምህርቷ ጋር በየወሩ የሚመክሩ ሲሆን  በልጆቻቸው ለውጥ ደስተኛ መሆናቸውን ተናገረዋል፡፡

በማክሰኝት ቁጥር አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት 122 የቅድመ መደበኛ ህጻናት በመማር ላይ ሲሆኑ ጨዋታን መሰረተ ያደረገ ትምህርት ከተጀመረ ወዲህ አንድም ተማሪ ከትምህርት ቤት አለማቋረጡንና የአሳላሽ ቁጥርም መቀነሱን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት ነገስ አደራ ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጀንበር አዳነ የማክሰኝት ቁጥር አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን ተሞክሮ በሁሉም የወረዳው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለማስፋት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ለመምህራንን፣ የወላጅ ተወካዮችንና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ህጻናትን በጨዋታ ማስተማር ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ስልጠና የወስዱ ሲሆን ከ3 ሚሊዬን ብር በላይ የሚያወጡ የመጫዎቻ ቁሳቁሶች በዩኒሴፍ በድጋፍ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *