‹‹ የወደፊት የሀገር እጣ ፈንታ የሚወሰነው በትምህርት ብቻ ነው ፡፡ ›› ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2016 ዓ.ም በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የዕውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እንደተናሩት፤ ትምህርት ለተሻለ ህይወት ማዘጋጃ ብቻ ሳይሆን ህይወትም ጭምር ነው፡፡ ውድ ተማሪዎቻችን የወደፊት ህልማችሁን ለማሳክት ከፍተኛ ውጤት አምጥታችሁ ለዚህ ቀን በመብቃታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ እኛም በእናንተ ኮርተናል ብለዋል፡፡
የምርጦች ምርጥ የሆናችሁ ውድ ተማሪዎቻችን ዛሬ የምንሰጣችሁ ሽልማት ለተከታይ ወንድሞቻሁና እህቶቻሁ አርኣያ በመሆን ሀገራችሁን ወደ ብልፅግና እንድታሻግሩና አለኝታ እንድትሆኑ ነውም ብለዋል፡፡
የወደፊት የሀገር እጣ ፈንታ የሚወሰነው በትምህርት ብቻ ነው ያሉት ሃላፊዋ፤ ድህነትን የምናሸንፍበት ዋነኛ መንገድ ትምህርት በመሆኑ ዛሬ ላይ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ማስተማር የሁሉም ሃላፊነት ነው ብለዋል፡፡
የለውጡ መንግስት አዲስ የትምህርት ስርዓት ቀርጾ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ በዚህም አበርታች ውጤት መጥቷልም ብለዋል ሃላፊዋ፡፡
እንደ ክልል ከ2014 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም በተከታታይ በሦስቱ ዓመታት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስደው ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች በቅደም ተከተል 3 ነጥብ 6፣ 4 ነጥብ 1 እና 6 ነጥብ 6 ፐርሰንት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም በክልሉ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱት 95 ሽህ 879 ተማሪዎች ውስጥ 187 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 49ኙ ሴቶች መሆናቸውን አክለዋል፡፡
በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በክልሉ 574 ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ይህም እንደ ሀገር 2ኛ ደረጃን እንድንይዝ አድርጎናል፡፡ ይህ ውጤት የመጣውም ከተማሪዎቹ ትጋት በተጨማሪ የትምህርት ማህበረሰቡ፣ ወላጆች እና አመራሩ በጋራ ባደረጉት ርብርብ ነው ብለዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም ለትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል ሲሉ የተናሩት ሃላፊዋ ለውጤታማነቱ ሁሉም የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት ከመንግስት ጎን በመሆን የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ክቡር አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ ከፍተኛ ውጤት ላመጣችሁ ተማሪዎች፤ ውጤቱ እንዲመጣ የበኩላችሁን ድርሻ ለተወጣችሁ መምህራን፣ ወላጆች እና በየደረጃው ያላችሁ አመራሮች ከፍተኛ ምስጋና ይገባችኋል፡፡ እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
ትምህርት በሁሉም ሀገር ሰብአዊ ልማትን ለመገንባት የሚያስችል እንደሆነ ያብራሩት ርእሰ መስተዳድሩ፤ ሳይንስና ቴክኖሎጅን በቅጡ እንድንረዳና ግብረገባዊ ስነ-ባህርይን የምንገነባበት መሳሪያም ነው ብለዋል፡፡
የአደጋዎች ሁሉ አደጋ የትምህርት ስርዓቱ ላይ የሚደረግ ጫና ነው፡፡ ትምህርት የፖለቲካ ማስፈፀሚያ እየሆነ መጥቷል ሲሉም አክለዋል፡፡
በክልሉ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ተማሪዎችና መምህራን የችግሩ ሰለባ ሆነዋል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ እርስ በእርስ መገዳደል አንድ ቦታ ላይ መቆም እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም እንደ ክልል ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች በሽልማት መርሐ ግብሩ የገንዘብ፣ የምስጋናና የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ክቡር አረጋ ከበደን ጨምሮ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ክቡር አብዱ ሁሴን፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ የማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፍስሃ ደሳለኝ፣ ተሸላሚ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆች እና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *