በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
============================
በጎንደር ከተማ ቀበሮ ሜዳ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ሕጻናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
ድጋፉ የተሠባሠበው በውጭ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሲኾን ስዊዲን ሀገር የሚኖሩት ወይዘሮ ሊሊ በላይ የተባሉ ግለሰብ አስተባብረውታል።
ድጋፉን ያስረከቡት አቶ አለባቸው በላይ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ስለመደረጉም ተናግረዋል።
ድጋፉን ከተረከቡ ተማሪዎች መካከል ናትናኤል ክብሮም እና ሙሉነሽ ደርሶ የተበረከተላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለትምህርታቸው ውጤታማነት አጋዥ ነው ብለዋል።
ለድጋፉ ምሥጋና ያቀረቡት የቀበሮ ሜዳ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ አስተባባሪ መላሽ ታከለ ይህን መሰሉ ድጋፍ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት በር ከፋች እንደኾነም ተናግረዋል።
ተማሪዎች በርትተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተመሳሳይ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
6 ሺህ 250 ወገኖች በመጠለያ ጣቢያው ተጠልለው እንደሚገኙ የተናገሩት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የተፈናቃዮች አሥተባባሪ መላኩ ገብሬ ከ3 ሺህ በላይ የሚኾኑት ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት ናቸው ብለዋል።
ሕጻናቱ በወቅቱ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ደግሞ ይህን መሰሉ ትብብር ወሳኝ በመኾኑ ድጋፉን ላደረጉ አካላትም ምሥጋና አቅርበዋል።
ለ3 ሺህ 300 ተማሪዎች የደንብ ልብስን ጨምሮ አንድ ደርዘን ደብተር፣ እስክርቢቶ እና እርሳስ እንደሚደርስ አቶ መላኩ ተናግረዋል።
በቀጣይም ከተማ አሥተዳደሩ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
አሚኮ