የአማራ ክልል የትምህርት ንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በትምህርት ዘርፉ የደረሰውን ጉዳት እና የሚያመጣውን አደጋ መረዳት አስፈላጊ ነው ብለዋል። ትምህርት ለረጅም ጊዜ ሲታመም እና ሲሰነካከል ቆይቷል፤ ከግጭቱ በፊትም ችግር ውስጥ የነበረው የትምህርት ጉዳይ በግጭቱ ምክንያት ደግሞ የበለጠ ተጎድቷል ነው ያሉት።
ትምህርትን ከገባበት ችግር ለማውጣት ዘላቂ የኾነ ሥራ እና ቁርጠኝነት ይፈልጋል ብለዋል። ጽንፈኛ ኃይሉ የመንግሥትን ህልውና አሳጣበታለሁ ብሎ የተጠቀመበት መንገድ ትምህርት መኾኑንም ገልጸዋል። ትምህርትን ለክፉ ዓላማ ተግባር እንደተጠቀመበትም ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ ትምህርት ሲነካበት መቆጣት አለበት ነው ያሉት። ትምህርት የየትኛውም አካል ቀዳሚ ተግባር መኾን እንደሚገባውም ገልጸዋል። የትምህርት መዘጋት ማለት ትምህርት ቤቶች በሥራ ላይ አይደሉም ማለት ብቻ አይደለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ጉዳቱ ከዚህ ባሻገር ነው ብለዋል።
“በትምህርት ላይ የደረሰው ጉዳት የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ ነው”ብለዋል። በትምህርት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመፍታት አቅደን መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት። በዕቅድ እየጠፋ ያለውን ዘርፍ በዕቅድ ማዳን አለብን ብለዋል።
ባለሙያዎች ዘርፉን በሙያቸው ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። መሪዎች ለትምህርቱ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም አሳስበዋል። የሙያ ማኅበራት እና ሌሎችም ትምህርትን መደገፍ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቶችን የማስተማር ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል ። የትምህርት ቤቶችን ጉድለት መለየት እና መፍትሔ መዘየድ እንደሚገባም አመላክተዋል። የትምህርት ሥራ ቅንጅት እና ትብብር እንደሚጠይቅም ገልጸዋል። በቅንጅት እና በፍጥነት በትምህርት ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ መቀልበስ ይጠበቃል ነው ያሉት።