የአማራ ክልል የትምህርት ንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር የክልሉን የትምህርት ችግሮች ለመፍታት የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል። በክልሉ የተፈጠረው የትምህርት ችግር ከፍተኛ መኾኑን ተረድተናል ነው ያሉት።
በትምህርት ላይ የደረሰው ጉዳት ለአማራ ክልል ሕዝብ ታሪክ የማይመጥን መኾኑንም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ ሚና አለው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ ይቀጥላል፣ ከገጠመው ችግርም እንደሚወጣ አምናለሁ ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት በችግር ውስጥም ኾኖ ለመምህራን የሰጠው ትኩረት የሚመሰገን መኾኑንም ገልጸዋል። የመምህራን ሚና ትውልድን የመገንባት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ወቅታዊ ችግር እና ቅሬታ የትውልድ ግንባታው እንቅፋት ሊኾን አይገባም ብለዋል።
መምህራን መስዋዕትነት እየከፈሉም ቢኾን የትውልድ ግንባታ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል። መምህራን ትውልድን ስለሚገነቡ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፣ ትምህርት ቤቶች ከግጭት ነጻ መኾን አለባቸው ብለዋል። ግጭት በሃሳብ የበላይነት መፈታት አለበት ያሉት ፕሬዝዳንቱ ተማሪን እና ትምህርት ቤትን መያዣ አድርጎ እታገላለሁ ማለት በዘላቂነት ትውልድን ይጎዳል ብለዋል።
“መምህራን ሥራቸውን እንዳይሠሩ እንቅፋት የሚኾኑ አካላት መወገዝ አለባቸው” ነው ያሉት። ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ነጻ መኾን አለባቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ወላጆች ልጆቻቸው የማይማሩ ከኾነ ተወዳዳሪ መኾን እንደማይቻል መገንዘብ አለባቸው ብለዋል።
እንደ ሀገር እና ሕዝብ ተወዳዳሪ መኾን የሚቻለው በትምህርት መኾኑንም ገልጸዋል። ወላጆች ልጆቻቸው ሳይማሩ ሲቀሩ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር መገንዘብ መቻል አለባቸው ነው ያሉት። መምህራን ማኅበረሰቡን ማስረዳት፣ ማሳመን እና ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የመማር ማስተማሩ ሥራ እንዲቀጥል፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ፣ የባከነ ጊዜ እንዲካካስ እና ተማሪዎች ዕውቀት እንዲያገኙ ማድረግ አለብን ነው ያሉት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *