የአማራ ክልል የትምህርት ንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በውይይቱ የተሳተፉ የወላጅ ተወካዮች ማኅበረሰቡ በትምህርት ላይ ያለውን ግንዛቤ ማስተካከል አለበት ብለዋል። ማኅበረሰቡ በትምህርት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በልኩ የተረዳው አይመስልም ነው ያሉት።
“ማዳበሪያ፣ ስኳር እና ዘይት ሲጠፋ በሚጮኸው ልክ ትምህርት ሲጠፋ አይጮህም። የሁሉም ነገር መነሻ ትምህርት መኾኑ ተዘንግቷል። ትምህርት ከሌለ ሁሉም እንደሌለ መረዳት አለብን” ብለዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ ሊቅ፣ አዋቂ፣ ተመራማሪ እና ተወዳዳሪ ልጅ እንዳያወጣ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ትምህርትን ማዳከም የአማራን ሕዝብ ማጥፋት እና ማሳነስ ነው ብለዋል።
የትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ለትምህርት ልዩ ትኩረት መሥጠት እንደሚገባውም ገልጸዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያዩ አቅጣጫ እያስቀመጡ መሥራት ይገባል ብለዋል። በትምህርት ዘርፉ ያለውን ችግር በተገቢው መረዳት እና ለመፍትሔው መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል።
በክልሉ ያለውን ትልቅ የምሁራን አቅም መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል። የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ መሪዎች መምህራንን መከታተል እና በተሟላ መንገድ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት።
በትምህርት ተቋሙ ሁለት ቦታ የሚረግጡ፣ የሚፈሩ፣ የሚሰጉ አካላት መኖራቸውንም ተናግረዋል። በጋራ ኾኖ ማጥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ትምህርት የመቀጠል እና ያለ መቀጠል ጉዳይ ነው ያሉት ኀላፊዋ ” በዚህ ዘመን ትምህርት የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይ ነው” ብለዋል። ሕዝቡ ከዚህ በላይ እንዳይጎዳ በቁርጠኝነት መታገል ይገባል ነው ያሉት።
መሪዎች ሕዝቡን ለትምህርት ማነሳሳት እና ልጆች እንዲማሩ ማድረግ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። ትልቁ መፍትሔ ከማኅበረሰቡ ጋር መግባባት እና አብሮ መሥራት መኾኑን ተናግረዋል። በመተባበር ሕዝብን ከችግር ማዳን እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
የራስን ችግር በራስ አቅም መፍታት፣ ኅብረተሰቡ ትምህርት ቤቶችን እንዲጠብቅ ማድረግ እና በቁርጠኝነት መሥራት አለብን ብለዋል።
በእኛ ማኅበረሰብ ዘንድ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ትልቅ ተቀባይነት አላቸው ያሉት ኀላፊዋ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር መወያየት ይገባል ነው ያሉት። ሁሉንም አቅም በማቀናጀት መጠቀም እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
የተማሪዎች ምዝገባ እስከ መጋቢት 30 ድረስ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ የትምህርት ቤቶችን ደኅንነት መጠበቅ እና ለመማር ማስተማር ምቹ ማድረግ ነው ብለዋል። የትምህርት ዙርፉን በሁሉም መልኩ መደገፍ፣ ነገን መልክ ማስያዝ እና ትውልድን ማስቀጠል አለብን ነው ያሉት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *