በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሰቲት ሁመራ ከተማ በሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች ለቅደመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በዛሬው ዕለት የምገባ ፕሮግራም አስጀምሯል።
በዚህም የዞኑ መሬት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱልዋስዕ አቡበከር፣የሰቲት ሁመራ ከተማ አሰተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ በላይ ፈለቀ፣በዞኑ ትምህርት መምሪያ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ቡድን መሪ አቶ አስረሳ ወንድይፍራው፣ የሰቲት ሁመራ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፍሁን ታደለ ተገኝተዋል።
የምገባ ፕሮግራም በትምህርት ቤቶች መካሄዱ ፍይዳው የጎላ ነው ያሉት የዞኑ መሬት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱልዋስዕ አቡበከር ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁም ይረዳል ብለዋል።
የበለፀጉ ሀገራት ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ሰተው በመስራታቸው የተሻለ ኑሮን እንዲኖሩ ከማድረግ ባለፈ በፈጠራ ስራቸው የተሻለ ትውልድን በመገንባት አስተዋጽኦ አድርገዋል ያሉ ሲሆን እኛም ታችኛው ትውልድ ላይ በትኩረት መስራት አለብን ብለዋል።
የምገባ ፕሮግራሙ የተለያዩ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ተማሪዎች የበታችነት ስሜትን በመቅረፍ በአኩልነት ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ጠቀሜታው የጎላ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ተሳትፎን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመው በዞኑ ሌሎች ከተማና ወረዳዎች ተሞክሮውን በመውሰድ የምገባ ፕሮግራሙን እንዲያስጀምሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለምገባ ፕሮግራሙ 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የከተማ አስተዳደሩ የመደበ መሆኑን የገለፁት የሰቲት ሁመራ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ በላይ ፈለቀ ምገባው በቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በሚገኙበት በአምስት ትምህርት ቤቶች እንደተጀመረ ገልፀዋል።
የምገባ ፕሮግራሙ የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን እስኪጠናቀቅ እንደሚቀጥል አንስተው በቀጣይ ዓመትም በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የምገባ ፕሮግራሙ ለመማር ማስተማር ሂደቱ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ያሉት አቶ በላይ ተማሪዎች በንቃት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያደርጋል ብለዋል።
በዞኑ ከ11 ሺህ በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ እንደሚገኙ ያነሱት በዞኑ ትምህርት መምሪያ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ቡድን መሪ አቶ አስረሳ ወንድይፍራው የምገባ ፕሮግራም በሁሉም ከተማና ወረዳዎች ለማስጀመር የንቅናቄ መድረክ ሲካሄድ መቆየቱን ገልፀዋል።
በዞኑ በወልቃይት ወረዳ በስድስት ትምህርት ቤቶች ከአልማ ጋር በመተባበር የምገባ ፕሮግራሙ ተጀምሮ የቆ መሆኑን ጠቅሰው በዛረው እለትም በሰቲት ሁመራ ከተማ በአምስት ትምህርት ቤቶች ለ5 መቶ 46 ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም መጀመሩን አንስተዋል።




