የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ ሀገራዊ የዜግነት ግዴታን ተቀብለው የገቡትን ሙያዊ ቃለ መሐላ ለመፈጸም እየሰሩ በሚገኙ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮችን ላይ ግድያ፣ እገታና እንግልት እየደረስባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለተማሪዎቻቸው ሁለተኛ ወላጅ የሆኑ መምህራን ትውልድን ወደ እውቀት ብርሃን ለማሸጋገር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እየሰሩ ቢሆንም በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት አስከፊ በደሎች እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መምህራን ለምን ታስተምራላችሁ በሚል ምክንያት እገታ፣ ግድያና መፈናቀል እየደረሰባቸው በመሆኑ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮን በእጅጉ ማዘኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ይህ ጉዳይ አስከፊ ጥቁር የታሪክ ጠባሳ የሚያስቀምጥ በመሆኑ መላው የክልላችን ተወላጅ፣ ኢትዮጵያዊንና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ደክሞ አዳሪውን፣ የህጻናትን የነገ ብሩህ ተስፋ የሚያለመልመውን ጋወን ለባሹን መምህር ተውት በማለት ሊያውግዘው የሚገባ ተግባር መሆኑን አቶ ደምስ አመላክተዋል፡፡
በአማራ ክልል በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ከ4 ነጥብ አምስት ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው፡፡ ከ3 ሽህ 6 መቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ ችግሩ በዚህ ከቀጠለ ነገ የአማራ እናት ከዩኒቨርሲቲ የምታስመርቀው ልጅ አይኖራትም፡፡ እንደእስካሁኑ አስተምረን በተለያዩ የአለም ክፍሎች የምናሰማራቸው ልጆች አይኖሩንም፡፡ የክልሉ ህዝብ በተለያዩ የሙያ መስኮች የሚያገለግሉት ልጆች ያጣል በዚህም ባለሙያዎችን ከሌላ አካባቢዎች ለማምጣት የሚገደድ መሆኑ አቶ ደምስ አብራርተዋል፡፡
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
- በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
- በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
- በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
- በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን