ዓለሙ ይታየው ይባላል። እስከ ዘጠነኛ ክፍል መጨረሻ ባለው የትምህርት ደረጃ ትምህርቱን ሲከታተል የቆየው ተወልዶ ባደገበት በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ነው።

ዓለሙ በ2015 ዓ.ም ከዘጠነኛ ወደ አስረኛ ክፍል ሲዘዋወር በአጠቃላይ ያስመዘገበው ውጤት 98 ነጥብ አምስት ከመቶ ነው። ምንም እንኳ ይሄን ያህል ውጤት ቢያስመዘግበብም ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ ከሚወደው፣ ለነገ ሕይወቴ መሠረት፣ ለቤተሰቦች መካሻ ይሆነኛል ካለው ትምህርት ነጠለው።

ግጭቱ በ2016 ዓ.ም ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነው እንዲከርሙ ማድረጉ ይታወሳል። ከዚህ ውስጥ ዓለሙ ይገኝበታል። በዓመቱ ዘግይቶም ቢሆን ትምህርት ይጀመራል የሚል ተስፋን በማንገብ የዓመቱን እያንዳንዷን ቀን የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን ሊያግዙ የሚችሉ መማሪያ መጻሕፍትን፣ አጋዦችን እና ቀድመው ከተማሩ ተማሪዎች የሚያገኛቸውን የማስታወሻ ደብተሮች ሲያጠና አሳልፏል። የ2016 የትምህርት ዓመትንም በጸጥታ ስጋት ታጅቦ፣ ነገር ግን ዛሬን ደርሶ ትምህርቱን እንደሚቀጥል ተስፋን በመሰነቅ ለእያንዳንዱ የትምህርት አይነት ራሱን መምህር፣ መኖሪያ ቤቱን እንደ ትምህርት ቤት ቆጥሮ ሲዘጋጅ ከረመ።

ሦስት ሺህ 667 ትምህርት ቤቶች በተዘጉበት እና ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት በተነጠሉበት የ2017 የትምህርት ዓመት ግን ከትምህርት ርቆ ላለመክረም ሲል ማቄን ጨርቄን ሳይል ጉዞውን ወደ ባሕር ዳር ከተማ አደረገ። ዓለሙ ከአንድ ዓመት የትምህርት መቋረጥ በኋላ የአሥረኛ ክፍል ትምህርቱን በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያስቀጠለ ይገኛል። የቀደመ ጉብዝናውንም አስቀጥሎታል። በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ከሚመካባቸው ቀዳሚ ተማሪዎች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል። በግማሽ ዓመቱ ያስመዘገበው ውጤትም 96 ነጥብ ዘጠኝ ከመቶ ነው።

ዓለሙ በትምህርት ቤቱ ከፍተኛውን ውጤት ሲያስመዘግብ በክልሉ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ ዳፋ ሳይለቀው፣ እንዳውም ተስፋ ቆርጦ ከትምህርት ገበታ ለመሰናበት ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ባደረገበት ወቅት መሆኑ ጥንካሬውን እና የዓላማ ጽናቱን በግልጽ የሚያሳይ ነው።

ዓለሙ በዚህ ዓመት በእጅጉ መፈተኑን ያስረዳል። ከአርሶ አደር ቤተሰቦች የተገኘው ዓለሙ አባቱን የሦስተኛ ክፍል ተማሪ እያለ በሕይወት ማጣቱ ዛሬ ላይ አቅሙ በኢኮኖሚው እንዲፈተን አድርጎታል:: ነገር ግን እናቱ ባላት አቅም ልክ ደግፋው የጀመረውን ትምህርት ከዳር አድርሶ ነገን እንዳያይ የጸጥታ ችግሩ በእጅጉ ፈተና እንደሆነበት ተናግሯል::

የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አለመኖር እና የባንክ አገልግሎት መቆራረጥ የቤት ኪራይ ለመክፈል፣ ምግብ ለማሟላት እና አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁስ አሟልቶ ትምህርቱን ለማስቀጠል አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ እንዳደረገው ተናግሯል:: ያም ሆነ ይህ ግን ዓለሙ የአንደኛውን ወሰነ ትምህርት በግንባታ ቦታዎች አፈር በማንሳት፣ ከገበያ ወደ ቤት ተሸክሞ በማድረስ በሚያገኘው ገቢ ራሱን እየደጎመ ትምህርቱን አጠናቋል::

ዓለሙ ተስፋ ሳይቆርጥ ዛሬን የደረሰው ጊዜውን ከፋፍሎ በመጠቀሙ እንደሆነ ይናገራል:: ከትምህርት ሰዓት ውጪ ያለውን ጊዜውን የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን ለመሥራት፣ ለጥናት እና ለእረፍት ከፋፍሎ በመጠቀሙ ዛሬ ላይ ለውጤት በቅቷል:: “ማንኛውም ተማሪ ከእኔ ብዙ ነገር መማር ይችላል፤ ዓላማ ማስቀመጥ፣ ለዓላማ መሰጠት እና ነገን አቅርቦ መመልከት ለውጤት ያበቃል” በማለትም ለመሰሎቹ ምክሩን አስተላልፏል::

ዓለሙ የትምህርት አቀባበሉ ሳይቀንስ ቀሪ ዓመታትን በድል አጠናቆ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመቀላቀል ጊዜውን እያባከነበት ያለውን የኢኮኖሚ አቅም የሚሸፍንለት አካል ይፈልጋል:: የትምህርት ቤቱ መምህራን እያደረጉለት ያለውን ድጋፍ አመስግኗል:: በቀጣይም አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲደግፉት፣ ሌሎች አካላትም በገንዘብ እና በተለያዩ ነገሮች እገዛ እንዲያደርጉለት ጠይቋል::

በትምህርት ቤቱ የአካል ብቃት (Physical Education) መምህሩ ስዩም ፈንታው ተማሪ ዓለሙ የትምህርት ቤቱ ጠንካራ እና ለሌሎች ተማሪዎችም በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን መስክረዋል:: በክፍል ውስጥ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች፣ ተሳትፎው፣ ሁሉንም ፈተናዎች ሙሉ በሙሉ በመሥራት የሚታወቅ እንደሆነም ገልጸዋል:: በሥነ ምግባሩም ምስጉን ሲሉ ጠርተውታል:: ተማሪ ዓለሙ ለሀገር የሚጠቅም ዕውቀት ያለው በመሆኑ አሁንም የሚጎድሉበት ብዙ ነገሮችን ደፍኖ በነጻነት ዓላማውን እንዲያሳካ አቅም ያለው ማንኛውም ግለሰብም ይሁን ድርጅት ሊደግፈው እንደሚገባ ጠይቀዋል::

 

የፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ወይዘሮ ደመቁ ዋለ በበኩላቸው ተማሪ ዓለሙ የአንደኛውን ወሰነ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና ከወሰደ በኋላ የኢኮኖሚ ችግር እንዳጋጠመው ጠቅሶ ወደ ትውልድ ቀየው ሊመለስ መሆኑን እንዳመለከተ አስታውሰዋል:: “በቀሪ ጊዜያትም ደብተር እና መጻሕፍትን እያነበብሁ ከርሜ በዓመቱ መጨረሻ ለፈተና ብቻ እንድመጣ ቢደረግ” ብሎ እንዳመለከት ርእሰ መምህሯ ተናግረዋል:: ትምህርት ቤቱም እንደተቋም በሚችለው አቅም እንደሚደግፈው፣ ሌሎች እገዛዎችም እንደሚመቻቹለት በማሳመን እስካሁን በትምህርት ገበታው ላይ እንዲቆይ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል::

ትምህርት ቤቱ ተማሪውን ማጣት ስለማይፈልግ እገዛ እንደሚያደርግለትም ርእሰ መምህሯ አረጋግጠዋል:: ነገር ግን ከትምህርት ቤቱ የሚደረግለት ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ሌሎች አካላትም የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉለት ርእሰ መምህሯ ጥሪ አቅርበዋል::

 

በኲር የመጋቢት 2017 ዓ.ም ዕትም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *