የጥበብ፣ የፍቅርና የመተሳሰብ መገኛ በሆነችው ወሎ፤
በርካታ የእውቀት ልሂቃንን ባፈረው አንጋፋው የደሴ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሰዎችን ስሜት የሚማርክ፣ ቀልብን የሚገዛ፣ ከተፈጥሮ ጋር የሚያስተሳር፣ መነሳሳትን የሚፈጥር አንድ ልዩ ክፍል አለ። ይህ ክፍል በተለያዩ አስደሳች የስዕልና የቅርጻቅርጽ ስራዎች የተሞላ ነው።
በክፍሉ ውስጥ ያሉ ስዕሎችና ቅርጻቅርጾች ተፈጥሮ፣ ባህል፣ ታሪክና አዳዲስ እሳቤዎችን የሚያንጸባርቁ አይነ ግቡ ናቸው።
እንዚህን ስዕልና ቅርጻቅርጾች ከሰሩት አሰልጣኝ መምህራን መካከል ሁሴን ሀሰንና ቀለመወርቅ ተገኘ ይገኙበታል። ከነዚህ አሰልጣኝ መምህራን ጋር በስዕልና ቅርጻቅርጽ ስቱዲዮአቸው ተገኝተን ስለ ስዕል፣ ዲዛይንና ቅርጻቅርጽ ጥበብ እንደሚከተለው ተጨዋውተናል።
የስዕል ጥበብን ለ11 ዓመታት በማስተማር ከ600 በላይ ተማሪዎችን ማፍራቱን የነገረን ሁሰን ሀሰን ሁሌም በክፍል ውስጥ ተማሪዎች ጋር ከመገናኘቱ በፊት መርጃ መሳሪያዎችን በስዕልና ቅርጻቅርጽ ሰርቶ እንደሚያስቀምጥ ይናገራል። ይህ ተግባሩም ተማሪዎችን የበለጠ ለማወቅና በተግባር ለመስራት ጉጉት እንዲያድርባቸው እንደሚያደርግ ገልጾልናል። ተማሪዎቹ በየጊዜው በስቱዲዮ ውስጥ በሚያደርጉት ልምምድ አስደናቂ ስዕሎችና ቅርጻቅርጾችን በመስራት የተዋጣላቸው ባለሙያዎች ሆነው እንደሚመረቁ ይናገራል። በርካታ ምሩቃን የራሳቸውን ስራም ፈጥረዋል።
መምህር ቀለመወርቅ በቡርሹ ቀለም ነክሮ ሸራ ላይ ሀሳቡን ለመግለጽ እንዳዋሀደ መሸቶ የተከራየው ቤት ተዘግቶበት ያውቃል። ስዕል እርጋታን ይፈልጋል የሚለው ቀለመወርቅ የሰዓሊ ዋና ስራው በቡርሽ ማውራት በመሆኑ ሰፊ የእይታ አድማስና አካባቢን መረዳት እንደሚጠይቅ ይናገራል። በስዕሎቹ ውስጥ ተፈጥሮን፣ የማህበረሰብ አኗኗርን፣ እድገቱን፣ ታሪክና ባህል ይንጸባረቃሉ።
ሰዓሊዎቹ ለስዕልና ቅርጻቅርጽ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ምሳ ሰዓታቸውን ጨምሮ ያላቸውን ትርፍ ሰዓት በስዕል ስራ ያሳልፋሉ። ዛሬ ላይ የስዕልና ቅርጻቅርጽ ስራቸው ከማስተማር አልፎ ሕይወታቸውን የሚደጉሙበት የስራ እድል ፈጥሮላቸዋል። ስዕሎቻቸው ተወዳጅነትን ስላተረፉ የገቢ ምንጭ ሆነዋል።
በተጨማሪም ጥበበኞቹ መምህራን የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ስዕሎችን በመሳል ውብ ሳቢና ማራኪ እንዲሆኑ በማስቻል የማህበረሰብ አግልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
የስዕል ትምህርት የማይደግፈው የትምህርት አይነት የለም የሚሉት መምህራኑ በስዕልና ቅርጻቅርጽ ጥበብ ለየትኛውም የትምህርት አይነት መርጃ መሳሪያ ማዘጋጀት እንደሚቻል ያምናሉ።
ተማሪዎች በቀላሉ አካባቢያቸውን እንዲገነዘቡ ለማስቻል የስዕልና ቅርጻቅርጽ ጥበብ ወሳኝ ነው። ነገ መሀንዲስ የሚሆነው ሰው በህጻንነቱ አካባቢውን ሲገነዘብ ንድፍንና ቀለም ቅብን ሲማር የተዋጣለት ባለሙያ እንዲሆን ያስችለዋል።
የስዕልና ቅርጻቅርጽ ጥበብ የህጻናትን አካላዊ እድገት፣ የቋንቋ ችሎታና አካባቢን የመረዳት አቅምን ያዳብራል። በስዕልና ቅርጻቅርጽ ጥበብ የሰለጠኑ ባለሙያዎች የትምህርት ቤት አካባቢን ለመማር ማስተማር ምቹ በማድረግ ከአካባቢ በሚገኙ ቁሳቁሶች መርጃ መሳሪያን በማዘጋጀት ትልቅ ሚና እየተወጡ መሆኑን መምህራኑ ይገልጻሉ።
ሰርተው በማሳየት ለተማሪዎቻቸው አርዓያ የሆኑት መምህራኑ ነገ ብሩህ ተስፋ ይታያቸዋል። ለስዕልና ቅርጻቅርጽ ጥበብ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት የስዕል መክሊት ያላቸው ህጻናት በልጅነታቸው ተስጥኦቸውን አውቀው እንደ ያለምሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ፣ ለማ ጉያና መሰል ሰዓሊያንና ጥበበኞችን ማፍራት።
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau




