





*******
የአማራ ልማት ማኅበር 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ እና የአልማ ጠቅላላ ጉባኤ ሠብሣቢ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ፣ የትምህርት ቢሮ ኀላፊ እና የአልማ ሥራ አመራር ቦርድ ሠብሣቢ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ፣ የትምህርት ቢሮ ኀላፊ እና የአልማ ሥራ አመራር ቦርድ ሠብሣቢ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) አልማ የትብብር እና የመደጋገፍ ምሳሌ፣ የአማራ ክልል ሕዝብም መገለጫ ነው ብለዋል። አልማ በ32 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በርካታ ማኅበራዊ ክፍተቶችን እየሞላ የሚጓዝ ጠንካራ ማኅበር መኾኑንም ገልጸዋል።
“አልማ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር የሚለውን የአበው ብሂል በትክክል የተረዳ፣ የመተባበርን እና የአንድነትን ፋይዳም በተግባር ገልጦ ያሳየ ነው” ብለዋል።
ማኅበሩ በ1984 ዓ.ም “ሺህ ኾነን እንደ አንድ፣ አንድ ኾነን እንደ ሺህ” በሚል መሪ መልዕክት ሲቋቋም የሕዝባችንን የመልማት ጥያቄዎች ለመመለስ፣ የተማረ የሰው ሀብት ለማፍራት እና በሁሉም ዘርፍ የለማ ክልል ለመፍጠር ያለመ ነበት ነው ያሉትንና ። ይህ እንዲሳካም በትጋት እየሠራ ነው ብለዋል።
አልማ መሠረታዊ የኾኑ የትምህርት እና የጤና መሠረተ ልማቶችን ከመገንባት በተጨማሪ የተለያዩ አደጋዎች በተፈጠሩ ጊዜም ለተጎጅዎች ቀድሞ የሚደርስ ማኅበር መኾኑን ተናግረዋል።
የሕዝቦችን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ የመንግሥት እጅ ብቻ በቂ እንዳልኾነ በመረዳት ተባብሮ የሚሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
አልማ ከመቀበል ይልቅ መሥጠት የሚያስደስተውን ሕዝባችንን እሴት በመጠቀም ለመረዳዳት እና ለአጋርነት የቆመ ማኅበር ነው ብለዋል።
የማኅበሩ አባላት የተለመደ የመስጠት እሴታቸውን በማጠናከር ከአልማ ጎን መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የአማራ ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መላኩ ፈንታ ማኅበሩ ሕዝባዊ የልማት ተሳትፎን በማረጋገጥ የትምህርት፣ የጤና፣ የሥራ ፈጠራ፣ የኑሮ ዘይቤ ማሻሻል እና መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቶችን ፍትሐዊ በኾነ መልኩ በመተግበር የልማት ጥረትን እየደገፈ ነው ብለዋል። አቃፊነት፣ ሕዝባዊነት እና አጋርነት የማኅበሩ መለያዎች መኾናቸውንም ጠቁመዋል።
ማኅበሩ ከ2012 እስከ 2016 ዓ.ም ከአጋር አካላት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ መሠብሠብ መቻሉንም ተናግረዋል።
ሀብቱም ለታቀደለት ዓላማ እንዲውል ይደረጋል ነው ያሉት። ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉም ገልጸዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ7 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የልማት ሀብት ማሠባሠብ መቻሉንም ገልጸዋል።
በ1ሺህ 198 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአጠቃላይ 2 ሺህ 952 የመማሪያ ክፍሎችን መገንባት መቻሉንም ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።አሚኮ
ሚያዝያ 07/2017 ዓ.ም
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
5.ቲክቶክ @amharaeducationbureau