የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪው ተማሪ ዘውዱ በለጠ በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ መማር ማስተማሩ በመቀጠሉ ተደስቷል።
ከነበረበት የፍርሃት አኹን የተሻለ ትምህርቱ ላይ ማተኮሩን ተናግሯል።
ክልላዊ እና ሀገራዊ ተፈታኝ ተማሪዎችን ከሌሎች የክልል ተማሪዎች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ በተመረጡ መምህራን እየተማሩ መኾናቸውንም ተማሪ ዘውዱ ገልጿል።
ቅዳሜ እና እሑድን ጨምሮ የማካካሻ ትምህርት እየተሰጠን ይገኛል ያለው ተማሪው ከመቼውም ጊዜ በተለየ ኹኔታ ምሽት ድረስ የቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ተጠቃሚ ኾነናል ነው ያለው።
ወላጆቼ የልጃችን ትምህርት ተቋርጦ ይቀር ይኾን? በሚል ሥጋት ያሳለፉትን ጭንቀት ጠንክሬ በመማር እና ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ለመካስ ተዘጋጅቻለሁ ብሏል ተማሪ ዘውዱ።
በባሕር ዳር ከተማ ፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዐይን አዲስ ጋሻው ደግሞ በ2018 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲ መግባትን ዓላማ አድርጋ እየበረታችን ነው።
ጊዜዋን በመርሐ ግብር ከፋፍላ እያጠናች እንደኾነም ገልጻለች። ቤተ መጽሐፍትን እና ቤተ ሙከራን አዘውትራ እንደምትጠቀምም አንስታለች፡፡
መምህራን ቅዳሜ እና እሑድን ጨምሮ የማካካሻ ትምህርት ይሰጡናል የምትለው ተማሪ ዐይን አዲስ የመለማመጃ ጥያቄዎችን ያሠሩናል፤ ይህም ከሀገራዊ ተማሪዎች ጋር ተወዳዳሪ እንዲንኾን የሚያግዝ ነው ብላለች።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ደመላሽ ታደሠ በዞኑ በ996 ትምህርት ቤቶች ለማስተማር ቢታቀድም በሰላም እጦት ምክንያት ትምህርት እየተሰጠ የሚገኘው በ158 ትምህርት ቤቶች ብቻ ነው ብለዋል። ይህ ጦርነቱ ያመጣው ዳፋ ነው ይላሉ።
ስድስተኛ ክፍል ላይ 4 ሺህ 246፣ ስምንተኛ ክፍል 4ሺህ 284 ለክልላዊ እና 12ኛ ክፍል ላይ 4 ሺህ 62 ተማሪዎችን ለብሔራዊ ፈተና ብቁ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለዚህም የቤተ መጻሕፍት፣ የቤተ ሙከራ፣ የአይሲቲ እና የኢንተርኔት ክፍሎችን የማመቻቸት ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት።
በተመረጡ መምህራንም የማካካሻ ትምህርት እና የመለማመጃ ጥያቄዎችን ማሠራቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።
የዞኑ ተማሪዎች በ2016 የትምህርት ዘመን ያመለጣቸውን ውጤት በዚህ የትምህርት ዘመን እንዲካካስ እየተሠራ ነው ብለዋል ምክትል መምሪያ ኀላፊው።
ዞኑም ያጣውን የተማሪ ሽፋን በውጤት ለመካስ ተግቶ እየሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ ቢሮው በ2017 የትምህርት ዘመን ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ቢያቅድም ክልሉ ባጋጠመው የሰላም እጦት ምክንያት ዕቅዱ አለመሳካቱን አንስተዋል።
ያም ኾኖ ክልሉ በተማሪ ምዝገባ ያላሳካውን በውጤት ለማካካስ ተግቶ እየሠራ ነው ብለዋል።
በግጭት ምክንያት ትምህርት ዘግይቶ በተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች የትምህርት ዓይነቶችን ለመሸፈን መምህራን ቅዳሜ እና እሑድን ጨምረው እያስተማሩ ነው ብለዋል። የማካካሻ ትምህርትም እየተሰጠ እንደኾነ ነው የገለጹት።
የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻልም የቤተ መጻሕፍት አጠቃቀም ተቀይሯል ያሉት አቶ መኳንንት፣ እንደ ኹኔታዎች አመችነት አብዛኛዎቹ ቤተ መጻሕፍት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ እያገለገሉ ነው ብለዋል።
በተማሪ ምዝገባ ያልተሳካውን ዕቅድ በውጤት ለመካስ ለተመረጡ የትምህርት ዓይነቶች የተመረጡ መምህራን ተመድበዋል ነው ያሉት።
በተለይ የ12ኛ ክፍል የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ብሎም ላቅ ያለ ውጤት ለማስመዝገብ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውለው የሚያድሩበት ጥናት መጀመሩን አቶ መኳንንት ተናግረዋል።
ሚያዝያ 15/2017
አሚኮ