የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሰሜን ሸዋ እና የምሥራቅ ጎጃም ዞኖችን፣ የደብረ ብርሃን እና የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደሮችን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።
ትምህርት ለሁሉም ነገር መሠረት ነው ያሉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ክልሉ በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥም ኾኖ በበርካታ አካባቢዎች የመማር ማስተማሩ ሥራ መቀጠሉን ጠቁመዋል።
ዶክተር ሙሉነሽ በተያዘው የትምህርት ዘመን በተለይም ባለፉት ዘጠኝ ወራት አበረታች ሥራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት። በምዝገባ ያላሳካነውን እቅድ አፈጻጸም በተማሪዎች ውጤት ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም የትምህርት መሪ በጋራ እየሠራን ነው ብለዋል።
በመምህራን፣ ወላጆች እና የትምህርት አጋር አካላት ጥረት በክልላዊ እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል።
መማር ማስተማሩን በመደገፍ ውጤታማ ለመኾን ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ እንደ ሀገር በእውቀት እና በሥነ ምግባር የታነፀ ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት የሁሉም ርብርብ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
ዶክተር ሙሉነሽ በአፈጻጸም ግምገማው ላይ ባስተላለፉት መልዕክትም “በውስብስብ ችግር ውስጥ ኾነንም ታሪካዊ ኀላፊነታችንን በመወጣት ተማሪዎችንን ውጤታማ ማድረግ ይገባናል” ብለዋል።
ሚያዝያ 19/2017
አሚኮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *