በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ እሔን ያሉት ትምህርት ቢሮው በጎንደር ከተማ እያካሄደ በሚገኘው የዘጠኝ ወር የግምገማ መድረክ ሲሆን በትምህርት ስርዓቱ የገጠመንን ፈተናዎች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አንስተዋል።
በተያዘው የትምህርት ዘመንን በክልሉ ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎችን ለመስተማር ታቅዶ ወደተግባር ቢጋባም አሁን ላይ በትምህርት ገበታ ያሉ ተማሪዎች ቁጥር 2.8 ሚሊዮን ብቻ መሆኑን ገልፀው ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች ደግሞ ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በትምህርት ሽፋኑ ያጋጠመንን ችግር በተማሪዎች ውጤት ለማካካስ እየተሰራ እንደሚገኝ ያነሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው በዚህ ዓመት ከወትሮው በተለየ መልኩ የክልልና የሀገር አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎችን የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የአዳር ጥናት ፕሮግራም በማዘጋጀት፣ የተሻለ ቤተ ንባብ አጠቃቀምን ተግባራዊ በማድረግ፣ የማካካሻ ትምህርትን በተመረጡ መምራን በመስጠትና በዩኒቨርስቲ መምህራን የስነልቦና እና የማነቃቂያ መርሀግብሮችን በመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ከህብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር በተመተባበር ከ900 በላይ የመማሪያ ህንፃዎች እየተገነቡ የሚገኝ ሲሆን በገንዘብ ደረጃ ከህብረተሰቡ የተገኘው ድጋፍ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክንዱ ዘውዱ በበኩላቸው በዞኑ የሚገኙ የክልልና ሀገር አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎችን በማብቃት በኩል አበረታች ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉና ሌሎች አካባቢዎችም ተሞክሮ እየወሰዱ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ካለፉት ዓመታት ልምድ መነሻ በማድረግ ተማሪዎችን በማብቃት እረገድ የአዳር ጥናትና ምገባን በመተግበር፣ የቤተሙከራ፣ የቤተ ንባብና የትምህርት ማበልጸጊያ ማዕከላትን በማጠናከር ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዞኑም በ29 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች ከ8ሺ300 በላይ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች የሚፈተኑ ሲሆን ከ29 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተናውን እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።
ከህብረተሰቡና ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በተገኘ ድጋፍ የተለያዩ የትምህርት ግብዓቶችን በሟሟላት እንዲሁም የመምህራን አቅም በማሳደግ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን የተናገሩት ደግሞ የጎንደር ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ነጋሽ ናቸው።
ኃላፊው አክለውም በጎንደር ከተማ በሚገኙ 16 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች የሚፈተኑ ከ3 ሺ በላይ ተማሪዎች ለፈተና በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመድረኩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የክልልና ሀገር አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎችን በማዘጋጀትና በማብቃት እንዲሁም ለፈተና ዝግጁ ከማድረግ ጋር ተያይዞ በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ ግምገማ ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ትምህርት ቢሮው በጎንደር ከተማ ባዘጋጀው የዘጠኝ ወራት ግምገማ የጎንደር ቀጠና የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊዎች ናቸው።
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን
5. በቲክቶክ ገፃችን @amharaeducation bureau