ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየሠራ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ በ2017 ትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ጥረት እያደረገ መኾኑን አስታውቋል።
በ2017 የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ተማሪዎች፣ መምህራን ፣ ወላጆች እና የትምህርት ቤተሰቦች ቀሪ ጊዜያትን በአግባቡ ለመጠቀም እየተረባረቡ ነው።
ከ7 ሺህ 800 በላይ ተማሪዎችን የሚያስፈትነው የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያም ዘንድሮ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ጥረት አድርጌያለሁ ብሏል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ዋስይሁን ብርሃኑ ለአሚኮ በሰጡት መረጃ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ በተግባር የታገዘ ትምህርት መስጠት፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ ማድረግ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ ቤተ መጻሕፍትን ሁልጊዜ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ እና የተማሪዎች የአዳር ጥናትን ማስጀመር ጥቂቶቹ እንደኾኑ ነው ያስገነዘቡት፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጸጋዬ እንግዳወርቅ ትውልድ የመፍጠር ሂደቱ በሰላም እጦት ቢፈተንም ተማሪዎች በተሻለ ውጤት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲገቡ በይዘት እና በሥነልቦና ጠንካራ ለማድረግ ተሞክሯል ነው ያሉት።
አሚኮ በኮቱ ካርል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝቶ የተማሪዎች ዝግጅት እና የመምህራን ድጋፍ ምን እንደሚመስል ተመልክቷል።
ተማሪዎች በቡድን እና በተናጠል በቂ ዝግጅት እያድጉ መኾኑንም መገንዘብ ችሏል።
ተማሪዎቹ በሰጡት ሀሳብ የተሻለ ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ማኩራት የሚያስችላቸውን ውጤት ለማምጣት ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በፈተና ወቅት ተረጋግተው በተዘጋጁበት ልክ የቀረበላቸውን ጥያቄ በመመለስ የተሻለ ነገር ለማምጣት ተስፋ አድርገው ሙሉ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙም ነው የገለጹት።
የትምህርት ቤቱ መምህራን እና የአሥተዳደር ሠራተኞችም ተማሪዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲኾኑ በቅርበት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ለውጤታማነቱ ግን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።