ተማሪ ቴዎድሮስ ብርሃኑ ይባላል በባህር ዳር ከተማ በግዮን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ተማሪ ቴዎድሮስ ለሳይንስና ቴክኖሎጅ ልዩ ፍቅር አለው፡፡
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ እያካሄደ በሚገኘው የተማሪዎች የፈጠራ ስራ ኤግዚቪሽን ላይ ያቀረበው የፈጠራ ስራ የብዙዎችን ትኩረት ስብቧል፡፡
ተማሪ ቴዎድሮስ ብርሃኑ እራሱ በሰራቸው ድሮንና አውሮፕላን አማካኝነት በሚለቀቅ ድምጽ የአንበጣ መንጋን የሚያባርር ቴክኖሎጅን ሰርቷል፡፡ የአበጣ ወረረሽን ሲከሰት ከ30-50 ኪሎ ኸርዝ በሆነ የድምጽ ፊሪኮንሲ ሲለቀቅበት አካባቢውን ለቆ እንድሚበር የሚገልጸው ተማሪ ቴዎድሮስ ድምጹ ሲለቀቅ ንቦችንና አካባቢ የማይረብሽ መሆኑን ገልጿል፡፡
በፈጠራ ስራዎቹ ሁሉ የቤተሰቦቹና የትምህርት ቤቱ ድጋፍ እንደማይለየዉ የሚናገረው ተማሪ ቴዎድሮስ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎቹን በአማራ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጅ፣ በኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴርና በተለያዩ ቦታዎች በማቅረብ እውቅና ማበረታቻ ማግኘቱን ነግሮናል፡፡
ተማሪ ቴዎድሮስ ብርሃኑ ወደፊት በአቬሽን ዘርፍ አለምን የሚጠቅሙ የራሱን የፈጠራ ቴክኖሎጅ መፍጠርን ያልማል፡፡
እንደ ተማሪ ቴዎድሮስ አይነት ባለራዕይ የፈጠራ ልጆችን ለማፍራት ትምህርት ቤቶች ሚናቸው ጉልህ ነው፡፡ በተለይም የሳይንስና ቴክኖሎጅ ክበባትን ማጠናከርና ተማሪዎችን ማበረታታት ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን ወደ ተግባር በመቀየር የመማር ማስተማር ስርዓቱን ለማሳደግና ለማጎልበት ያግዛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *