መምህራን በትምህርት ስርዓቱ ላይ የደረሰውን ስብራት በመጠገን ትውልድ የመገንባት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
“ትውልድ በመምህር ይቀረፃል ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ ቃል በደብረብርሃን ከተማ ከሁሉም ትምህርት ቤት ከተውጣቱ መምህራን ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ መሆኑ፣በትምህርት ስራ ውስጥ የሃይማኖት አባቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ ቢፈጠር፣ለመምህራን በጊዜ ገደብ የመንግስት ቤት ተሰርቶ የሚጠቀሙበት እድል ቢመቻች የሚል ሀሳብ በውይይቱ ቀርቧል፡፡
የኑሮ ውድነት፣የመምህራን ጥቅማጥቅም አለመሟላት፣የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ አለመሆን፣የግል ትምህርት ቤት መምህራን የቤት መስሪያ ቦታ አለማግኘት፣የመምህራን ሸማች ማህበር አለመቋቋም ፣ባለው ሃብት በፍትሃዊነት አለመጠቀም፣የሚሉ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ተነስተዋል፡፡
ስርዓተ ትምህርቱ ሲሻሻል መምህራን ስልጠና ባለማግኘታቸው በአተገባበሩ ላይ አሉታዊ ተጽኖ ማሳደሩ፣የግል ትምህርት ቤት መምህራን ስልጠና አለማግኘት ችግር፣የመምህራን ዝውውር አለመኖር፣የአካቶ ትምህርት፣ የሙዚቃና የሙያ ትምህርት መምህራን እጥረት እና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች በመድረኩ ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የደብረብርሃን ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መቅደስ ብዙነህ እንደገለጹት ውይይቱ ጠቃሚ ግብዓት የተገኘበት መሆኑን አንስተው ተቋማቸው የራሱን ወስዶ ለመፍትሄው እንደሚሰራና በየደረጃው ለሚመለከታቸው እንደሚያቀርብ አመልክተዋል፡፡
በውይይቱ የታየውን አወንታዊ ቁጭት ወደ ተግባር መለወጥ፣ለውጡን በውል ተገንዝቦ ማስቀጠል፣ክፍተቶችን መሙላትና ያጋጠመውን የትምህርት ስብራት ተጋግዞ ማከም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡
ለዚህም መምህራን ተቀራራቢ ዕውቀት፣ክህሎትና አመለካከት መያዝ እንደሚጠበቅባቸውና የየድርሻቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ ባዬ አለባቸው በበኩላቸው እንደገለጹት የመድረኩ ተሳታፊዎች የተሰማቸውን በግልጽ መናገራቸው እጥረቶች እንዲታረሙና ጥናካሬዎች እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ስለሆነ አስተያየት ለሰጡት ሁሉ ክብር አለን ብለዋል፡፡
በአለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ያለውን ጫና ተቋቁሞ የለውጡ መንግስት በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኑ የሚበረታታና መምህራንም በቀጣይ ለውጡን ደግፈው ሊያስቀጥሉት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
በትምህርት ስርዓቱ ላይ ተደጋጋሚ ስብራት መድረሱን አንስተው ችግሩን ለማስተካከል መምህራን ድርብ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
የደብረብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ የተከበሩ በድሉ ውብሸት የውይይት መድረኩን ሲያጠቃልሉ እንደገለጹት ለሀገር ግንባታ የሁሉም ዜጋ አስተዋጽኦ አስፈላጊ ቢሆንም በትውልድ ግንባታ ስራ ውስጥ የመምህራን ሚና የላቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ የተነሱት ሀሳቦች ጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው በሙሉ ተወስደው በየደረጃው ምላሽ እንዲያገኙ ይሰራል ብለዋል፡፡
ከግል ትምህርት ቤት መምህራን መኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ ጋር በተያያዘ የሰራር መመሪያ ባይኖረውም ጥያቄው ፍትሃዊ ስለሆነ ከሚመለከተው አካል ጋር በቀጣይ ተነጋግረው ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰሩ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ከመምህራን የትራንስፖርት ሰርቪስ አገልግሎት፣የኑሮ ውድነት፣ህገ ወጥነትን መከላከልና ሌሎች ጥያቄዎች አስመልከቶ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ግንቦት 12/2017

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *