ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ ለመገንባት ከአጋር የልማት ድርጅቶች ጋር በጋራ እየተሠራ ነው።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ ከተማ በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የተገነቡ የትምህርት ተቋማትን እና የቴክኖሎጅ ግብዓቶችን ተመልክተዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራሽ ታደሰ በክልሉ በግጭት ምክንያት የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እና ግብዓቶችን ለማሟላት ከአጋር የልማት ድርጅቶች ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ተቋማትን መልሶ ከመገንባት በተጨማሪ የትምህርት ዘርፉን በዲጅታል ቴክኖሎጅ ለመደገፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ በኾነባቸው አካባቢዎች የኢንተርኔት እና የኮምፒውተር ግብዓት እየተሟሉ እንደኾነም ገልጸዋል።
ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የትምህርት እና የጤና ተቋማትን መልሶ በመገንባት እና የቴክኖሎጅ ግብዓቶችን በማሟላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑንም ተናግረዋል። እየተደረገ ላለው ሁለንተናዊ ድጋፍም አመስግነዋል።
ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት ከመገንባት በተጨማሪ በሳይንስ እና ቴክኖሎጅ የበቁ፣ ተወዳዳሪ እና ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት የትውልድ ግንባታ ላይም ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን የድርጅቱ ኮሙዩኒኬሽን ኀላፊ ምስክር ገበየሁ (ዶ.ር) አንስተዋል።
ለአብነትም በላሊበላ እና በዋግኽምራ አካባቢ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በርካታ ኮምፒውተሮችን እና ሌሎች የቴክኖሎጅ ግብዓቶችን በማሟላት የዲጅታል ላይበራሪ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረጉን ነው የገለጹት።
በሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ ከተማ ጉዳት ከደረሰባቸው የትምህርት ተቋማት መካከል የቅድስት መሰቀል ክብራ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነው።
የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ተስፋ ወዳጅ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ መማሪያ ክፍሎችን ከመገንባት በተጨማሪ 35 ኮምፒውተሮችን እና የተለያዩ ይዘት ያላቸው አጋዥ መጽሐፍቶችን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
የተደረገው ድጋፍም በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ይከሰት የነበረውን የመጽሐፍት እና የመማሪያ ክፍል እጥረት መፍታት ችሏል ነው ያሉት።
ተማሪዎች በሳይንስ እና ቴክኖሎጅ የላቀ ዕውቀት እንዲኖራቸው የሚያስችል በዲጅታል የተደገፈ የላይበራሪ አገልግሎት እየተሠጠ መኾኑንም ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቱ የአይሲቲ መምህር የኾኑት አሰፋ ደስታው የዲጅታል ላይበራሪ አገልግሎት መኖሩ ተማሪዎች እና መምህራን ከቴክኖሎጅ ጋር እንዲላመዱ እና ዘመኑን የዋጀ ዕውቀት እና ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው ብለዋል።
የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችም የድጅታል ላይበራሪ ተጠቃሚ መኾናቸው ስለ ሀገራቸው እና ስለ ዓለም ታሪካዊ ዳራ ሰፊ ግንዛቤ እና ዕውቀት እንዲኖራቸው ማስቻሉን ተናግረዋል።
በተለይም በኬሚስትሪ፣ በባዮሎጅ እና በፊዚክስ የትምህርት ዘርፍ የኬሚካል ውህዶችን ኮምፒውተር ላይ በተግባር በመማራችን በኬሚካል ውህደት ጊዜ የሚያጋጥመውን አድጋ ለመቀነስ አግዞናል ነው ያሉት።
በትምህርት ቤቱ ያለውን የኬሚካል እና የመጽሐፍት እጥረት ከመፍታት ባለፈ የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ክህሎትና ዕውቀታቸውን ለማሳደግ እንዳገዛቸው የገለጹት ተማሪዎቹ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ስላደረገው ድጋፍም አመሥግነዋል።
ግንቦት 12/2017